የአሰልጣኙን ውል ለማራዘም የተቃረበው አርሰናል ሁሊያን አልቫሬዝ እና ሞርጋን ሮጀርስን ማስፈረም ይፈልጋል

AMN ግንቦት 25/ 2018 ዓ.ም

ከ22 ዓመታት በኋላ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን አሸንፎ ደጋፊውን ጮቤ ያስረገጠው አርሰናል ፊቱን ወደ ቀጣይ ዓመት አዙሯል፡፡

በሊጉ ያገኘውን የበላይነት ይዞ ለመቀጠል ፣ በመለያ ምት ተሸንፎ ያጣውን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግን ወደ ሰሜን ለንደን ለማምጣት ከወዲሁ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡

የክለቡ ባለቤቶች በቅድሚያ ማድረግ የሚፈልጉት ጠንካራ ቡድን ገንብቶ የናፈቁትን የሊግ ዋንጫ ያመጣላቸውን አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታን ውል ማራዘም ነው፡፡ የ44 ዓመቱ አሰልጣኝ በመድፈኞቹ ቤት የሚያቆየው ውል በቀጣይ የውድድር ዓመት ይጠናቀቃል፡፡

አርቴታ አሁን ላይ ዓመታዊ 10 ሚሊየን ፓውንድ የሚያገኝ ሲሆን ቡድኑን ለአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ ሲያደርግ ደግሞ አምስት ሚሊየን ፓውንድ ጉርሻ ይበረከትለታል፡፡ የክለቡ ባለቤት የክሮንኬ ቤተሰቦች የስፔናዊውን አሰልጣኝ ደሞዝ ዕጥፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳሳዩ ቢቢሲ ስፖርት ዘግቧል፡፡

የክለቡ ሊቀመንበር ጆሽ ክሮንኬ ሚኬል አርቴታን ማቆየት የክለቡ ቀዳሚው ስራ እንደሆነ ተናግሮ ነበር፡፡ አርቴታ በአርሰናል የመቆየት ፍላጎት ስላለው ውሉን ያራዝማል ተብሎ የጠበቃል፡፡

ክለቡ የአሰልጣኙን ቆይታ ካረጋገጠ በኋላ ፊቱን ወደ ተጫዋቾች ግዢ እንዲሁም ሽያጭ ያዞራል፡፡ ክለቡ በተለይ የማጥቃት አማራጩን ለማስፋት ከአስቶንቪላ ሞርጋን ሮጀርሰን ፣ ከቦርንማውዝ ጁኒየር ክሩፒን እንዲሁም የአትሌቲኮ ማድሪዱ ሁሊያን አልቫሬዝን የማስፈረም ፍላጎት አሳይቷል፡፡

13 የፕሪምየር ሊግ ግቦችን አስቆጥሮ የበርካታ ታላላቅ የአውሮፓ ክለቦች አይን ውስጥ የገባው የ19 ዓመቱ አጥቂ ጁኒየር ክሩፒን ለመሸጥ ቦርንማውዝ እስከ 80 ሚሊየን ፓውንድ ይፈልጋል፡፡

የአርሰናል ትልቁ ህልም የሆነው የአትሌቲኮው ሁሊያን አልቫሬዝ እስከ 120 ሚሊዮን ፓውንድ ይጠራበታል፡፡ ሞርጋን ሮጀርስም ወጪው 100 ሚሊየን ፓውንድ የሚጠጋ ነው፡፡ አርሰናል እነዚህን ተጫዋቾች ለማስፈረም ከሌሎች ክለቦች ከባድ ፉክክር ይጠብቀዋል፡፡

ክለቡ ግዢዎቹን ለመፈፀም ተጫዋች መሸጥ ይጠበቅበታል። ክለቡ ባለፈው የውድድር ዓመት ለዝውውር ብቻ 250 ሚሊየን ፓውንድ ማውጣቱ ፣ ለወሳኝ ተጫዋቾቹ ደግሞ ደሞዝ አሻሽሎ ውል ማራዘሙ ስለሽያጭ እንዲያስብ ያስገድደዋል፡፡

ጋብርኤል ጄሱስ ፣ ሊአንድሮ ትሮሳርድ ፣ ጋብርኤል ማርቲኔሊ ፣ ኢታን ንዋኔሪ ፣ ክርስቲያን ኖርጋርድ ፣ ቤን ዋይት እና ሪስ ኔልሰን ክለቡ ሊሸጣቸው እንደሚችል የተጠቆሙ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review