በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአንድ ሀገር ጥንካሬ የሚለካው በድንበር ጠባቂ ሰራዊቷ ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ሰማዩን በመቆጣጠር አቅሟ ጭምር ነው። ጦርነት ከምድር ተነስቶ ወደ ጠፈር በተሸጋገረበት በዚህ ዘመን፣ የአየር ኃይል ለሀገር ህልውና ግንባር ቀደም ምሰሶ ሆኗል። ይህ ኃይል ለአንድ ሀገር ያለው ፋይዳ ከመደበኛ ወታደራዊ ዘመቻ አልፎ፣ የኢኮኖሚ ዋስትና፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጭ እንዲሁም የዲፕሎማሲ አቅም መገለጫም ነው።
የሀገርን ዳር ድንበር ለማስከበርና ሉዓላዊነትን ለማጽናት የአየር ኃይል ሚና የማይተካ መሆኑን የተረዱ ሀገራት፣ የቴክኖሎጂ እና የሰው አቅም ግንባታቸውን ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ኢትዮጵያ ለዚህ በማሳያነት ከሚጠቀሱ ጥቂት የአፍሪካ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዘጠና ዓመታትን ያስቆጠረ ቀደምትና አንጋፋ ተቋም ነው። ከሰሞኑም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የተመሰረተበት 90ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች አክብሯል። በእነዚህ ዓመታትም በርካታ ውጣ ውረዶችን እያለፈ አኩሪ ተግባራትን መፈጸም ችሏል፡፡
የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረበኣል ላይ ተገኝተው የተናገሩት ንግግርም ይህንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ “የኢትዮጵያ አየር ኃይል ኢትዮጵያን ለመድፈር ለሞከሩ ኃይሎች ሁነኛ መድኃኒት ሆኖ ሀገር ያጸና ተቋም ነው።” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
መቶ አለቃ በቀለ በላይ የቀድሞ ሰራዊትና ወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ አየር ኃይል ኢትዮጵያ በታሪኳ የገጠሟትን የውጭ ወረራዎች ለመቀልበስ የነበረው ሚና ታሪካዊ ነው። በተለይም በ1970ዎቹ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ወቅት፣ አየር ኃይሉ የጠላትን ወራሪ ኃይል በመምታት ረገድ የፈጸመው ገድል ዛሬም ድረስ በዓለም ወታደራዊ ታሪክ ውስጥ የሚጠቀስ ነው። ያኔ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጠላት ላይ ያሳየው የበላይነት የሀገሪቱን የግዛት አንድነት ለማስከበር ወሳኝ ድርሻ ነበረው።
መቶ አለቃ በቀለ፣ አየር ኃይል በርካታ ዓመታትን የተጓዘ፣ ለሉዓላዊነት መከበር ጉልህ ድርሻ ያበረከተ የሀገር ሃብት ቢሆንም ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበት እንደነበር ያስረዳሉ፡፡
ይሁንና ይላሉ መቶ አለቃ በቀለ በላይ፣ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በታሪኩ በርካታ ውጣ ውረዶችን ቢያልፍም፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወነው የሪፎርም ስራ ተቋሙን ከነበረበት የመፍረስ አደጋ አውጥቶ ወደ ዘመናዊነት ያሸጋገረ ትልቅ ርምጃ ሆኗል፡፡ ምክንያቱም የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ትኩረት ከሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ አየር ኃይል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

“የሪፎርሙ አስፈላጊነት የመነጨው ተቋሙ ካለበት ሀገራዊ ኃላፊነት አንጻር በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል እና በስትራቴጂክ ዝግጁነት ረገድ የነበሩበትን ክፍተቶች ለመሙላት ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት አየር ኃይሉ በአብዛኛው በሰው ኃይል ብቃት ላይ ብቻ የተመሰረተ እንጂ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ የላቀ አቅም አልነበረውም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አየር ኃይል የነበረውን ታሪክ ስለሚያውቁ በቁጭት ሪፎርም እንዲካሄድ ማድረጋቸው ከሰሞኑ የተመለከትነው ብቃት ላይ እንዲገኝ ሆኗል” በማለት መቶ አለቃ በቀለ አብራርተዋል፡፡
መቶ አለቃ በቀለ በላይ በቅርቡ በአየር ኃይሉ የተለያዩ ማዕከላት ተገኝተው ያለውን እንቅስቃሴ የታዘቡ ሲሆን፣ የተመለከቱት ለውጥ እጅግ አስገራሚ መሆኑን ገልጸዋል። “አየር ኃይልን ለመለወጥ ቀን ከሌሊት እየተሰራ ነው፤ ይሄን በአካል ተገኝቼ በአይኔ ተመልክቻለሁ” ሲሉ ሃሳባቸውን ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል አጋርተዋል፡፡
አክለውም “ይህ ግዙፍ የለውጥ ስራ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባለፈ፣ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ለሀገር ውስጥ ዜጎችና ለአፍሪካዊያን ሰፊ የልምድ ልውውጥ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል። የአየር ኃይሉ ዘመናዊነት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ላይ ዋና የጀርባ አጥንት መሆኑን በኩራት መመስከር ይቻላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ መቶ አለቃ በቀለ ገለጻ፣ ለውጡ በንግግር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የተከናወነ መሆኑን አይቻለሁ፡፡ አየር ኃይል በአሁኑ ጊዜ ከየትኛውም የውጭ ጠላት የሚቃጣን ጥቃት የመመከት አቅም አለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበዓሉ ላይ አየር ኃይሉ ኢትዮጵያን ከውጭ ጠላቶች በብቃት የመከላከል አቅም መገንባቱን አንስተዋል።እርሳቸው፣ “ከወዳጆቻችን ጋር በጋራና በትብብር ለመስራት ቁርጠኞች ነን። ለጠላቶቻችን ደግሞ በር መዝጋታችንን ማረጋገጥ ይገባናል፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ተኝተን የማናድር መሆናችንን ለማስገንዘብ እወዳለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።

አክለውም “ባለፉት ዓመታት ከገዛናቸው፣ ካሻሻልናቸው እና ከሰራናቸው ቴክኖሎጂዎች በላይ የሰው ኃይል ግንባታ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል፡፡ እንዲሁም አየር ኃይል በቀጣይ 5 ዓመታት አሁን ካለበት ደረጃ በእጥፍ ያድጋል” በማለት አስታውቀዋል፡፡
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በበኩላቸው በበዓሉ ላይ በታየው ትርኢት ላይ የተሳተፉ አብራሪዎቹ ያሳዩት የላቀ ብቃትና ጥበብ ከመደበኛው ወታደራዊ ተግባር ባሻገር የተቋሙን ዝግጁነትና የቴክኖሎጂ የበላይነት ለዓለም ያስመሰከረ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ተለዋዋጭ እየሆነ የመጣውን የጦርነት አውድ ተረድቶ የላቀ የመከላከል አቅም ያጎለበተ የሰው ኃይል መገንባት እንደተቻለም አክለዋል፡፡
በእርግጥም በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ የአየር ኃይል ትርጉም ከሰው ሰራሽ አውሮፕላኖች ወደ ሰው አልባ አውሮፕላኖች (Drones) እና ወደ ህዋ ቴክኖሎጂ እየተሸጋገረ ነው። አንድ ሀገር ህልውናዋ እንዲከበር፣ ሉዓላዊነቷ እንዲጠበቅ እና ህዝቦቿ በሰላም ወጥተው እንዲገቡ ጠንካራ፣ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የበለፀገ የአየር ኃይል መገንባት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ አየር ኃይል ባለፉት 8 ዓመታት በመንግሥት በተሰጠው ልዩ ትኩረት፤ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና በውጊያ መሠረተ ልማት የላቀ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ከታሪክ አኳያ ሲታይም ተቋሙ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስከበር ደሙንና አጥንቱን የገበረ፣ በቴክኖሎጂ ራሱን እያዘመነ ያለና ለቀጣናዊ ሰላም ዋስትና የሆነ ተቋም ነው።
በጊዜው አማረ