የወንዝ ዳር ልማቱ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር ምን ሚና አለው?

You are currently viewing የወንዝ ዳር ልማቱ ምቹ ከባቢን ለመፍጠር ምን ሚና አለው?

አቶ እንዳልካቸው አምባዬን ያገኘናቸው የግንፍሌን የወንዝ ዳርቻ ልማት ሲጎበኙ ነበር፡፡ ልማቱን በተመለከተ ለዝግጅት ክፍላችን ትዝብታቸውን እንዲህ ሲሉ ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ከወንዞች ጋር በመገናኘታቸው ለብክለት ተጋልጠው ቆይተዋል፡፡ ይህም ወንዞቹ ለሰዎች፣ ለእንስሳትና ለዕፅዋት ጤንነትና ደህንነት ጥቅም ከመስጠት ይልቅ ስጋት እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እንደ ቁርጡሚ ባሉ ወንዞች ዓሳ ይኖር እንደነበርና አሁን ላይ በተቃራኒው የዓሳ ዝርያዎች መጥፋታቸውን በማንሳት ወንዞች ምን ያህል ለሰውና ለእንስሳት አስጊ ሆነው እንደቆዩ ገልጸዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማዋ እየተካሄደ ያለው የወንዝ ዳርቻ ልማት አዲስ ገጽታን እንዲላበሱ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ ወንዞች ከስጋት ምንጭነት ተላቅቀው የመዝናኛ ማዕከል እየሆኑ ነው፡፡ ድሮ ሰው በወንዙ አጠገብ ሲያልፍ የነበረው መጥፎ ሽታ በአሁኑ ወቅት የለም፡፡ ከውበትም ባለፈ አሁን ንጹህ አየር ማግኘት እንደተቻለ ገልጸዋል። የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ምልከታም ይኸንኑ የሚያጠናክር ነው፡፡ አካባቢው በአረንጓዴ ልማት ተውቦ እና ለአይን የሚማርክ ሆኖ አግኝቶታል፡፡

አቶ ዋቢ ከድር ትውልድና እድገታቸው አዋሬ አካባቢ ሲሆን የግንፍሌ ወንዝንና አካባቢውን ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ ታዲያ ነፍስ አውቀው መጫወት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ወንዙ በትንሹም ቢሆን መቆሸሽ መጀመሩንና በአንጻሩ የቀበና ወንዝ ንጹህ ስለነበረ እየሄዱ ይዋኙ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ የግንፍሌ ወንዝም ቢሆን ድሮ ላይ ውሃው ንጹህ እና ልብስ ያጥቡበት እንደነበር ከወላጆቻቸው ይሰሙ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ የሰው ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ውሃው እየጠቆረና ለአፍንጫም የሚሰነፍጥ ሽታ እያመጣ፣ በሂደት ደግሞ ወደ ወንዙ የሚጣለው የቆሻሻ መጠን እየጨመረ ሲመጣ የውሃ መውረጃው መደፈኑን አስታውሰዋል፡፡

“ልማቱ ከዚህ ቀደም ለማየትም ሆነ በአካባቢው ለማለፍ አስቸጋሪ የነበረውን የወንዝ ዳርቻና አካባቢ ውብና ጽዱ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡ በተለይም ወንዞችን ከብክለት ነፃ በማድረግ ደህንነታቸው ተጠብቆ ለህዝብ መዝናኛነት እንዲውሉ አድርጓቸዋል፡፡ እኔ ራሴ እንደምታይኝ እየተዝናናሁበት ነው፡፡ ብዙ ጊዜዬን የማሳልፈው በዚህ ስፍራ ነው፡፡ በዚህ መልኩ ላሳልፍ የቻልኩት አካባቢው ንጹህና ምቹ ሆኖ በመልማቱ ስለሆነ መንግስትን ማመስገን እፈልጋለሁ” ብለዋል አቶ ዋቢ፡፡

ወይዘሮ ሙሉ እመቤት ተክለወልድ ወደ አዲስ አበባ የመጡት በ12 ዓመት እድሜያቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ቀደም ባሉት ጊዜያት የከተማዋ ወንዞች በቅጡም አይታዩም ነበር፡፡ ዙሪያቸው ባረጁና ባዘመሙ ቤቶች የታጀቡ ነበሩ። የሞተ ነገርን ጨምሮ የተለያዩ አይነት ቆሻሻዎች መጣያ ከመሆንም በላይ ሰዎች ይጸዳዱባቸው ስለነበር ስናልፍ በጣም ነበር ይሸቱ የነበረው፡፡ ከአካባቢው መቆሸሽ የተነሳም ፍጥነታችንን ጨምረን ነበር የምናልፈው፡፡ አሁን በዚህ መልኩ መጽዳት መቻላቸው ለሰውም ሆነ ለእንስሳት ምቾትን ፈጥሯል። አሁን ላይ ወንዙም አካባቢውም ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ልማቱ በጣም ነው የሚያስደስተው፡፡ ‘ለካ እንዲህ ፅዱ ማድረግ ይቻል ነበር’ እላለሁ፤ የድሮውንና የአሁኑን እያነጻጸርኩ ሳስብ፡፡ ይህንን ላሳየኝ አምላኬ ምስጋና ይግባው” ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡

ወጣት በረከት ይስጠኝም ከላይ የተሰጠውን ሃሳብ ይጋራል፡፡ “በወንዝ ዳርቻዎቹ የተሰሩት የመዝናኛ ስፍራዎች ጊዜአችንን በአልባሌ ቦታ እንዳናሳልፍ እና ንፁህ አየር እየወሰድን እንድንዝናና ዕድል ፈጥረውልናል” የሚለው ወጣቱ፣ ከዚህ ቀደም እነዚህ አሁን ንጹህና ውብ የወንዝ ዳርቻዎች የቆሻሻ መጣያና ለአይን ለማየትም ሆነ ለአፍንጫ የሚረብሹ እንደነበሩ በማስታወስ በዚህ ደረጃ ለምተው በመመልከቱ መደሰቱን ገልጾልናል፡፡

የወንዝ ዳርቻ ልማቱ ከስማርት ሲቲ ምሰሶዎች መካከል አንዱ የሆነውን ስማርት ከባቢን (Environment) በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው የሚናገሩት ደግሞ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሐይቅ፣ የውቅያኖስ፣ የባሕርና የወንዝ ልማት የውሃ ዳር ልማት ወይንም የወንዝ ዳር ልማት በመባል ይጠራል፡፡ የወንዝ ዳር ልማት የከተማ ግብርናዎችን በማስፋፋት ረገድ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለመዝናኛነትና ለቱሪዝም መስህብነት የሚውሉ ትላልቅ ሆቴሎች፣ ሎጂዎች፣ ሪዞርቶች፣ የመናፈሻና መዝናኛ ስፍራዎች እንዲኖሩ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደምረው የከተማውን ውበት ያስጠብቃሉ፡፡

ሌላው ከውሃ ጋር የተያያዘ ልማት ተፈጥሮን ያስጠብቃል፡፡ በወንዝ ዳር ልማትም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ልማት ማካሄድ ይቻላል፡፡ የተመረጡ ዛፎችን በመትከል አካባቢውን አረንጓዴ ማድረግ ይቻላል፡፡ የተመረጡ የዛፍ አይነቶችን እንዲሁም አረንጓዴ ስፍራዎችን ለማልማት ምንጩ የወንዝ ውሃ ነው፡፡

ዳንኤል (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ ውሃ ተኮር የሆነ የግብርና ልማት ዘላቂነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ቀደም ሲል ወንዞች ቆሻሻና ለአካባቢያዊ ብክለት መንስኤ ነበሩ፡፡ በወንዝ ዳርቻ ልማቱ ወንዞች ንጹህ ሆነዋል፤ መልሶ በመጠቀም ለልማት እየዋሉ ነው፡፡ ለቤት ውስጥ፣ ለግብርና እና ለኢንዱስትሪ የምንጠቀምበት እድል እየተፈጠረ ነው፡፡ አረንጓዴ፣ ውብና ለምለም የሆነ ብቻም ሳይሆን የአየር ንብረትንም የሚቋቋም የማይበገር ከተማ ከመፍጠር አንጻር ትልቁን ሚና ይጫወታሉ፡፡ አዲስ አበባም ይህንን እድል እየተጎናጸፈች ትገኛለች፡፡

አዲስ አበባ ቀደም ሲል በግንፍሌ፣ ቀበና እና በአቃቂ ወንዞቿ ስትጠቀም አልነበረም፡፡ አሁን ወንዞች እየለሙ ይገኛሉ፡፡ በሁሉም ዳርቻዎች ላይ አረንጓዴ ልማትና ልምላሜ እንዲሁም ለሰው ልጅ ተስማሚ በሆነ መልኩ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች፣ ሎጂዎች፣ ሪዞርቶች፣ ንግዶች፣ የመንገድ መሰረተ ልማትና የተለያዩ የከተማ አገልግሎቶች እየተፈጠሩላት ነው፡፡ በዚህም አዲስ አበባ የልማት ትንሳኤ ላይ እንደምትገኝ ዳንኤል (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

አሁን ላይ አዲስ አበባ ለስራ ፈጠራ፣ ለኢንቨስትመንትና ለቱሪዝም ልማት የስበት ማዕከል እየሆነች ነው፡፡ የወንዝ ዳርቻው ሜትሮፖሊታን ከተማ ሆና የምታገለግልበትን እድል እየፈጠረላት ነው፡፡ ወንዞች ለከተማ ልማት መረጋገጥ ወሳኝ ናቸው፡፡ በሌሎች ሀገራት ተሞክሮ ወንዝ ካለ ከተማ አለ፡፡ በእኛ ሀገር ተሞክሮ ግን ወንዝ ካለ ጫካ ነበር የነበረው፡፡ ውሃ ለሀገር ልማት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ በታሪክ ከተሞች የተመሰረቱት በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ነው፡፡ ለአዲስ አበባ ከተማ መመስረት ትልቁን ሚና የተጫወተው ፍል ውሃ እንደሆነ ዳንኤል (ዶ/ር) በማሳያነት አንስተዋል፡፡

“አንድ አካባቢ ለሰው ልጆች ምቹና ተስማሚ ሲሆንና ሲዘምን ስማርት ኢንቫይሮመንት (ከባቢ) ነው ይባላል። ከዚህ አንጻርም የአዲስ አበባ ከተማ የወንዝ ዳርቻ ልማት ወንዞችና አካባቢያቸው ጽዱና አረንጓዴ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ ጽዱና አረንጓዴ መሆናቸው ደግሞ አካባቢው ከብክለት ነጻ ሆኖ ንጹህ አየር እንዲነፍስ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ከማስቻሉም በዘለለ ምቹ፣ ተስማሚ እና ለመዝናኛነት የሚያገለግሉ አገልግሎቶች እንዲፈጠሩ በማድረግ ስማርት ኢንቫይሮመንት እንዲፈጠር የላቀ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ስማርት ኢንቫይሮመንት የከተማ ግብርናን እና ኢንቨስትመንት ከማሳደጉም በዘለለ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው መቃናት ወሳኝ ነው፡፡ በአዲስ አበባ አሁን ላይ እየታየ ያለውም ይኸው ነው፡፡ ለዚህም ነው አዲስ አበባ ዳግም ውልደት ላይ ትገኛለች የተባለው” ይላሉ ዳንኤል (ዶ/ር)፡፡

የአዲስ አበባ ስማርት ሲቲ ዕቅድ ላይ እንደተመላከተው፣ ስማርት ከባቢ የውሃ አቅርቦት፣ የቆሻሻ አወጋገድና አስተዳደር፣ የአየር ብክለት ቁጥጥር፣ የአረንጓዴ ቦታ፣ የኃይል አጠቃቀም ስርዓቶችን ማሻሻልን ይመለከታል። መዲናዋ በረጅም ጊዜ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከተማዋን አረንጓዴ፣ ፅዱና ከአካባቢ ጋር የተስማማች ለማድረግ ታቅዷል፡፡

በለይላ መሀመድ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review