AMN -ጥር 23/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አዲስ አበባ ሰላም የሰፈነባትና የተረጋጋ ንግድ ያላት ከተማ እንድትሆን እየሰራ ላለው ስራ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ሎተሪ አገልግሎት ዕውቅና እና የ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ስጦታ ተበርክቶለታል።
ዕውቅናው በተለይም አዲስ አበባ የዲፕሎማቶች መነሀሪያና የአፍሪካውያን መለያ ከተማ በመሆኗ፤ የተለያዮ ዓለምና አህጉር አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት እንድታከናውን ባለስልጣን ላበረከተው አስተዋፅኦ የተበረከተ ስለመሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሎተሪ አገልግሎት ገልጿል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ የንግድ ስርዓት የከተማዋን ልማት የሚመጥንና ጤናማ እንዲሆን ያበረከተው አስተዋፅኦም ለሽልማት እንዳበቃው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሎተሪ አገልግሎት አስታውቋል።
ሽልማቱን የተቀበሉት የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ም/ስራ አስኪያጅ አቶ ንጋቱ ዳኛቸው ፤ ባለስልጣኑ በአዋጅ የተቋቋመበትን ሀላፊነት በሚገባ ለመወጣት በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ እንቅስቃሴ ሰላማዊ፣ ህግን መሰረት ያደረገና ለነዋሪዎች እንዲሁም ለጎብኝዎች ምቹ እንዲሆን ከተለያዮ ተቋማት ጋር በአጋርነት የሚሰራው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሎተሪ አገልግሎት ለባለስልጣኑ ለሰጠው ዕውቅናና ሽልማት አመስግነው ይሁም ለተሻለ ስራ የሚያነሳሳ መሆኑንም ገልፀዋል።
በንጉሱ በቃሉ