AMN – ጥር 23/2018 ዓ.ም
ገበያው የሚፈልገውን በእውቀትና በክህሎት የበቃ ትውልድን ለማፍራት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን የስልጠና አቅም ለማሳደግ በተሰራው ስራ አበረታች ውጤት መመዝገቡን የአዲስ አበባ ከተማ የትምህርትና ስልጠና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።
ባለስልጣኑ በሙያ ተቋማት ላይ ያከናወነው የኢንስፔክሽንና በዕውቅና ፍቃድ ዕድሳት ሰነድ ትንተና እንዲሁም ዘርፉን ለማገዝ በተደረጉ ጥናቶች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ አካሒዷል።
ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ዘመኑ የሚፈልገውን ዓለም ዓቀፍ ተወዳዳሪ ትውልድን ለማፍራት ግንባር ቀደም ተዋናይ ናቸው ያሉት የባለስልጣኑ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ታጋይቱ አባቡ ተቋማቱን ለማብቃት በተደረገ የክትትልና ድጋፍ ስራ አዳጊ ውጤቶች እየተመዘገ ይገኛል ብለዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በየጊዜው በመንግስትና የግል ቴክኒክና ተቋማት ላይ በተለይም ንድፈ ሐሳብን ከተግባር ያሣለጠ ስልጠና መስጠት የሚያስችሉ የግብአት፣ብቁ የሰው ኃይል ጨምሮ የስልጠና ሒደትን በተመለከተ የክትትልና የቁጥጥር ስራን በትኩረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ማሰልጠኛ ተቋማቱ ተግባር ተኮር ስልጠናን ለመስጠት ያሉባቸውን ጉድለቶች እንዲያሟሉ በማድረግ በክህሎት ተወዳዳሪ ትውልድን ለማፍራት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ተቋማቱ የሚሰጡን ስልጠና ለማላቅ ከኢንደስትሪዎች ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ድጋፍ እየተደረገ ነው ያሉ ወ/ሮ ታጋይቱ ህብረተሰቡ ውስጥ ስለ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት ያለው አመለካከት እየተሻሻለ ቢሆንም አሁን ስራ ስለሚፈልግ ሁሉም ባለድርሻ የግንዛቤ ማሳደግ ስራው ላይ በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ ገልፀዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረገው ክትትልና ድጋፍ ስራ ስኬታማ ስራዎችን በማከናወን ደረጃቸውን ላሻሻሉ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ዕውቅናና ሽልማት አበርክቷል።
በሔኖክ ዘነበ