AMN ጥር 25 ቀን 2018 ዓ.ም
አርሰናል በ10 ነጥብ እርቆ የፕሪምየር ሊግ ዋናጫ የማሸነፍ አቅም አለው ሲል የስካይ ስፖርት ተንታኙ ጂሚ ሬድናፕ ተናገረ፡፡ በሊቨርፑል ፣ በቶተንሃም ሆትስፐርስ እና በሌሎች ክለቦች ተጫውቶ ያሳለፈው ጂሚ ሬድናፕ የዋንጫው ፉክክር አብቅቷል ሲል ተናግሯል፡፡
የሰሜን ለንደኑን ክለብ በቅርብ እርቀት ሲከተሉ የነበሩት ማንችስተር ሲቲ እና አስቶንቪላ ነጥብ መጣላቸው ፉክክሩ እንዲያበቃ አስተዋፅኦ አድርጓል ብሏል፡፡
“እንደኔ ሀሳብ የዋንጫ ፉክክር አብቅቶለታል፡፡ አርሰናል በስምንት ወይም በ10 ነጥብ እርቆ ዋንጫውን ያነሳል ፤ ይህን ካላደረገ በጣም እገረማለሁ፡፡” ሲል ጂሚ ሬድናፕ ሀሳቡን አካፍሏል፡፡

“ከዚህ ቀደም ዋንጫ ያላነሳ ስብስብ ስላላቸው በመጠኑ የመረበሽ ስሜት ይታይባቸዋል፡፡ አሁን ግን ያን ያህል ስጋት ስለሌለባቸው ዘና ማለት ይችላሉ፡፡” ብሏል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ ማንችስተር ሲቲም ይሁን አስቶንቪላ አርሰናልን የመቋቋም አቅም እንደሌላቸው ጂሚ ሬድናፕ ተናግሯል፡፡
ትናንት በተደረጉ የ24ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች አስቶንቪላ በሜዳው ቪላ ፓርክ በብሬንትፎርድ 1ለ0 ሲሸነፍ ፣ ማንችስተር ሲቲ ከቶተንሃም ጋር 2ለ2 መለያየቱ ይታወሳል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ