የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በነፃ የሚሳተፉበት የብስክሌት ፌስቲቫል በአራዳ ፓርክ ሊካሄድ ነው

You are currently viewing የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በነፃ የሚሳተፉበት የብስክሌት ፌስቲቫል በአራዳ ፓርክ ሊካሄድ ነው

AMN ጥር 27 ቀን 2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ፣ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን እና የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከ” ነፍ ” ኮሚኒኬሽን ጋር በመተባበር ማንኛውም የአዲስ አበባ ነዋሪ ተሳታፊ የሚሆንበት “ብስክሌት በአዲስ ፌስቲቫል ” ማስጀመሪያ መርሐግብር ይፋ አድርገዋል።

ፕሮግራሙ የፊታችን እሁድ ከጠዋቱ 2:00 እስከ ረፋዱ 5:00 ድረስ እንደሚከናወን ዛሬ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተጠቅሷል።

በሁለት ዙር በተሰራው የኮሪደር ልማት 241 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ መሰራቱን ያስታወሱት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አስመራው ብርሀኔ ፌስቲቫሉ የብስክሌት መጠቀም ባህልን የሚያበረታታ እና በከተማዋ የተሰሩ መንገዶችን አጠቃቀም ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በአዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች ለማስተዋወቅ እንዲህ አይነት ስፖርታዊ ኩነቶች ወሳኝ መሆናቸውን የጠቀሱት የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ቢኒያም ታዬ የብስክሌት በአዲስ የውድድር መድረክ ለከተማዋ የስፖርት ቱሪዝም ፍሰት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በወንዝ ዳርቻ ልማት ከለሙት አካባቢዎች አንዱ በሆነው አራዳ ፓርክ መነሻው ራስ መኮንን ድልድይ የሆነው ፌስቲቫል ህፃናት ፣ ወጣቶች ፣ አዋቂዎች ፣ ስፖርተኞች ፣ ታዋቂና ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች በነፃ ይሳተፉበታል ተብሏል።

በአሸናፊ በላይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review