አዲስ አበባን በማታ የማታንቀላፋና ከጨለማ የተላቀቀች ከተማ ለማድረግ እየሰራን ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing አዲስ አበባን በማታ የማታንቀላፋና ከጨለማ የተላቀቀች ከተማ ለማድረግ እየሰራን ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ጥር 29/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ይገኛል። በጉባኤው ላይ የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተከናወኑ ዋና ዋና የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን የእቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ለምክር ቤቱ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡

ከንቲባዋ በሪፖርታቸዉ ፤ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን ተደራሽ፣ ጥራት ያለውና የህዝቡን እርካታ የሚያረጋግጥ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። በተለይም በሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት፣ በመንገድ መብራት፣ በኤሌክትሪክ አቅርቦት፣ በጽዳት አስተዳደር እንዲሁም በእሳትና አደጋ ስጋት አመራር ረገድ የተቀናጀ የአፈጻጸም ስርዓት መዘርጋቱን ጠቁመዋል።

የከተማዋን ደህንነትና ውበት ለመጠበቅ የመንገድ መብራት አስተዳደር በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ መደረጉን የጠቀሱት ከንቲባዋ፣ በዚህም ፈጣን የጥገና ስርዓት መዘርጋቱን አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም ጨለማ የነበሩ ኮሪደሮችንና አካባቢዎችን በብርሃን ለመሸፈን የተሰሩ ስራዎችን አብራርተዋል፡፡

በዚህም፤በ7 ሺህ 579 የመብራት ፖሎች ላይ የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ የዝርጋታ ስራ ተከናውኗል።

8 ሺህ 432 መብራቶች ጥገና የተደረገላቸው ሲሆን፣ 968 የሚሆኑት ደግሞ ወደ ዘመናዊው የኤል.ኢ.ዲ (LED) ቴክኖሎጂ ተቀይረዋል።

14 ግዙፍ የመብራት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት የበቁ ሲሆን፣ ሌሎች 23 ፕሮጀክቶች ደግሞ በቅርብ ክትትል ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ስራዎች የከተማዋን የመንገድ መብራትና የደህንነት ካሜራ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻላቸዉን እና አዲስ አበባ በማታ የማታንቀላፋና ከጨለማ ሙሉ በሙሉ የተላቀቀች ደህንነቷ የተጠበቀ ከተማ እንድትሆን ማድረግ መሆኑን በሪፖርታቸዉ ጠቅሰዋል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review