AMN – የካቲት 05/2018 ዓ.ም.
በአዲስ አበባ የሚከናወኑት 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባዔን አስመልክቶ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው ኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚካሔደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን በማሳየት ያለፈውን ብቻ ሳይሆን የመጻዒው የፓን አፍሪካኒዝም አርአያነቷን አጠናክራ መቀጠሏን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአሕጉራዊ አንድነትና የፓን አፍሪካኒዝም ማሳያ የሆነው የዘንድሮውን የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ እንዲሁም ጎን ለጎን የሚካሄደውን ታሪካዊውን የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባዔ በድምቀት ለማካሔድ ዝግጅቷን ማጠናቀቋንም ነው የገለጹት።
የካቲት 6/2018 ዓ.ም የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባዔ በቅድሚያ የሚካሔድ ሲሆን በቀጣዩ ቀን የካቲት 7/2018 ዓ.ም. ደግሞ 39ኛ ጊዜ የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ እንደሚካሔድ ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።
የዘንድሮው የመሪዎቹ ጉባዔ”የ2063 አጀንዳ ግቦችን ለማሳከት ዘላቂ የውሃ አቅርቦት እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የጤና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ” በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚካሄድ በጋዜጣዊ መግለጫው ተገልጿል።
ከዚህ አንጻር ሀገራችን ለአፍሪካውያን ልታቀርባቸው ከምትችላቸው በርካታ ተሞክሮዎች መካከል በአረንጓዴ ልማት አሻራ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ50 ቢሊየን የሚሻገር ችግኝ በመትከል የደን ሽፋንን ከ17 ወደ 23 በመቶ በማሳደግ ለዘላቂ ልማት ያለንን ቁርጠኝነት ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል።
እንዲሁም ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የውሃ፣ የነፋስ እና የጸሐይ ታዳሽ ኃይል አማራጮችን በመጠቀም የኢነርጂ ፍላጎቷን በማሳደግ ከራስ ፍላጎት ባለፈ ለጎረቤት ሀገራት ጭምር መትረፍ መቻሏንና እንዲሁም በነዳጅ የሚሰሩ ተሽከርካዎችን በመከልከል ለታዳሽ ኢነርጂ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ማሳየቷን አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገልጸዋል።
በከተማ የኮሪደር እና በወንዝ ዳርቻ ልማት ከተሞችን ጽዱና ውብ በማድረግ የአካባቢ ብክለትን የቀነሱ ደማቅ ከተሞችን የመፍጠር ጥረት በአዲስ አበባ ተጀምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ተግባራዊነቱ እንደቀጠለም ሚኒስቴር ዲኤታው ተናግረዋል።
ከፕላስቲክ የጸዳ አካባቢ ለመፍጠር የአንድ ጊዜ የፕላስቲክ መያዣዎችን በመከልከል ለዘላቂ ልማት እና ለአካበቢ ጥበቃ ያላትን ቁርጠኝነት ዳግም ማስመስከሯን የምታጋራቸው ተሞክሮ መሆናቸውን አቶ ተስፋሁን በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
በያለው ጌታነህ