ጉባኤው የኢትዮጵያ እና የጣሊያንን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ አጋርነት የለወጠ ወሳኝ ሁነት ነው- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing ጉባኤው የኢትዮጵያ እና የጣሊያንን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ አጋርነት የለወጠ ወሳኝ ሁነት ነው- የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

AMN የካቲት 7/2018

2ኛው የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ እና የጣሊያንን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ አጋርነት የለወጠ ወሳኝ ሁነት ነው ሲል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት 2ኛው የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ ለኢትዮ-ጣሊያን ስትራቴጂካዊ አጋርነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት 2ኛውን የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ አስመልክቶ ያወጣው ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ለኢትዮ-ጣሊያን ስትራቴጂካዊ አጋርነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተው የ2ኛው የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ!

የኢትዮጵያ የውጭ ፖሊሲ ከገቢራዊ ዲፕሎማሲ ወደ ስልታዊ አጋርነት በመሸጋገር፣ ሀገራዊ ጥቅሟን ከቀጠናዊ ትስስር ጋር ያስታረቀበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን።

በአፍሪካ የዲፕሎማሲ መዲና አዲስ አበባ፣ የካቲት 6 ቀን 2018 ዓ.ም የተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ፣ በአፍሪካና አውሮፓ አህጉራት መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያሸጋገረ ኩነት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ይህ ጉባኤ ከጣሊያን ምድር ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ፣ በተለይም በኢትዮጵያ መካሄዱ፣ ሮም ለአፍሪካ የሰጠችውን ስትራቴጂካዊ ክብደት እና ኢትዮጵያ በአህጉሩ ያላትን የመሪነት ሚና የሚያጎላ ነው።

ጉባኤው ከተለመደው የ”ለጋሽ እና ተቀባይ” አስተሳሰብ በመውጣት፣ “እኩል አጋርነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ ስር የተቃኘ መሆኑ፣ በአውሮፓ እና በአፍሪካ መካከል ያለውን የጂኦ-ፖለቲካዊ እና የኢኮኖሚ ትስስር እንደገና ለመቀየስ ያለመ መሆኑን ያመላክታል።

የኢትዮጵያ እና የጣሊያን ግንኙነትን በታሪክ ዐውደ ስንመለከት፣ በአድዋ ጦርነት እና በፋሽስት ወረራ ወቅት ከነበረው የቅራኔ ታሪክ ተላቆ፣ አሁን ላይ ወደ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት የተሸጋገረበትን ሂደት እናስተውላለን።

በተለይም ከ1947ቱ የሰላም ስምምነት በኋላ የተገነባው ግንኙነት፣ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና በጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ መሪነት ወደ ላቀ “ስትራቴጂካዊ አጋርነት” አድጓል።

ይህ የታሪክ ሽግግር ለዛሬው ጉባኤ ስኬት የመሰረት ድንጋይ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ያላት ግንኙነት በባህል፣ በታሪክ እና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስር የጠለቀ መሆኑ ጉባኤው ተጨባጭ ውጤት እንዲያመጣ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የዚህ ጉባኤ እምብርት የሆነው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ የተዋወቀው “የማቲ ዕቅድ”፣ ለአፍሪካ ልማት የተመደበውን የ5.5 ቢሊዮን ዩሮ የኢንቨስትመንት ማዕቀፍ መሰረት ያደረገ ነው።

ይህ ዕቅድ በዋናነት ትኩረት ያደረገባቸው ስድስት ምሰሶዎች—ማለትም ኢነርጂ፣ ግብርና፣ ውሃ፣ ጤና፣ ትምህርት እና መሠረተ ልማት—ከኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳዎች ጋር በቀጥታ የሚተሳሰሩ ናቸው።

ጣሊያን አፍሪካን የአውሮፓ የኢነርጂ ማዕከል ለማድረግ ያላት ፍላጎት፣ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል (እንደ ኮይሻ እና ህዳሴ ግድብ) ያላትን እምቅ አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው። ይህ የኢነርጂ ትስስር ኢትዮጵያን የኃይል ላኪ፣ አውሮፓን ደግሞ የንጹህ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግ የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ነው።

ከኢትዮጵያ አንጻር የጉባኤው ፋይዳ በዲፕሎማሲያዊ ድል ብቻ የሚወሰን አይደለም። በኢኮኖሚው ረገድ ጣሊያን ለአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግር እና ለጤናው ዘርፍ ማሻሻያ (በቅርቡ የተፈረመውን የ15 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ጨምሮ) የምታደርገው አስተዋጽኦ በቀጥታ የዜጎችን ህይወት የሚነካ ነው።

የጣሊያን ኩባንያዎች በቡና፣ በቆዳ ውጤቶች እና በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ወደ ኢትዮጵያ ማምጣታቸው፣ የኢትዮጵያን ምርቶች ወደ አውሮፓ ገበያ በስፋት ለማቅረብ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንደመሆኗ፣ ይህንን ጉባኤ ማስተናገዷ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተሰሚነት ከፍ የሚያደርግ እና እንደ አውሮፓ እና አፍሪካ “ድልድይ” ሆና እንድታገለግል ድርብ እድል የሚሰጥ ነው።

በአዲስ አበባ የተካሄደው 2ኛው የአፍሪካ-ጣሊያን ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ እና የጣሊያንን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ አጋርነት የለወጠ ወሳኝ ሁነት ነው።

የጉባኤው ስኬት ከኢነርጂ እስከ ግብርና የወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ላይ ተመሰረተው የተነደፉት የትብብር መስኮች በፍጥነት ወደ ተግባር ተቀይረው የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ሲችሉ ነው።

ኢትዮጵያ ይህንን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የቀጠናውን ሰላም በማጽናት እና የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት፣ ከጣሊያን ጋር ያላትን ግንኙነት ለብሔራዊ ጥቅሟ ማስከበሪያ እና የአፍሪካ የጋራ ልማትን ማላቂያ አድርጋ የምትጠቀመብት ይሆናል ።

ኢትዮጵያ አህጉራዊ ትስስርን በተግባር በመምራት፣ ለበለጸገች አፍሪካ ብርሃን የምትፈነጥቅ የለውጥ ችቦ መሆኗን ዛሬም እያረጋገጠች ትገኛለች፡፡

የኢፌዴሪ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት!

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review