ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ይበልጥ ማጠናከሯ ተገለጸ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላትን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ይበልጥ ማጠናከሯ ተገለጸ

AMN የካቲት 8 ቀን 2018 ዓ.ም

መንግሥት ከታዋቂ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያለውን ስትራቴጂያዊ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከሩን አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ከሚገኘው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) እና ከአረብ ባንክ ለኢኮኖሚ ልማት በአፍሪካ (BADEA) ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተከታታይ ውይይቶችን አድርገዋል።

ሚኒስትሩ ከአረብ ባንክ ለኢኮኖሚ ልማት በአፍሪካ ፕሬዝዳንት አብዱላህ አልሙሰይቢህ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ በኢትዮጵያ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከልም በዋነኝነት በቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ግንባታ፣ በኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣በመንገድ ልማት እና በንግድ ፋይናንስ ዘርፎች ትብብርን ለማሳደግ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ የCOP32 ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤን ለማስተናገድ ለምታደርገው ዝግጅት የሚውሉ የአየር ንብረት ተከላካይ መሠረተ ልማቶችን በጋራ ለመገንባት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተወያይተዋል።

ከአፍሪካ ልማት ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ኬቪን ካሪዩኪ (ዶ/ር) ጋር በተደረገው ውይይት፣ በኢነርጂ ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉ ሪፎርሞች ላይ ገለጻ ተደርጓል። ባንኩ በ “Mission 300” አማካኝነት የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያሳድግ የተጠየቀ ሲሆን፣ ዶ/ር ካሪዩኪ ባንኩ የኢትዮጵያን የኢነርጂ አማራጮች ለማስፋትና ቀጠናዊ ትስስርን ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ከዓለም አቀፍ የግብርና ልማት ፈንድ (IFAD) ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጄራርዲን ሙኬሺማና ጋር በነበራቸዉ ቆይታም የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ግብርና፣ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ማሳደግ፣ እና አዲስ በተጀመረው የአርሶ አደር መር መስኖ ልማት ፕሮግራም ላይ ተወያይተዋል፡፡

እነዚህ ከፍተኛ የሥራ ግንኙነቶች ኢትዮጵያ ከልማት አጋሮቿ ጋር ያላትን የጋራ መተማመን የሚያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ፣ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መድረክ (COP32) ላይ ለምትጫወተው የመሪነት ሚና ትልቅ አቅም እንደሚፈጥሩ ገንዘብ ሚኒስቴር ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review