ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፤ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

You are currently viewing ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፤ የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዝግጅት ማድረጉን ገለጸ

AMN- የካቲት 11/2018 ዓ.ም

የፊታችን ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ካለፉት የምርጫ ተሞክሮዎች በተሻለ ሁኔታ እንዲከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገልጿል።

ምክር ቤቱ የምርጫው ሂደት ዲሞክራሲያዊ እንዲሆንና ፓርቲዎች በነጻነት እንዲሳተፉ ምህዳሩን የማስፋት ስራ እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

የጋራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ማሩ ጃኔ ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት፣ ፓርቲዎች እራሳቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ እጩዎቻቸውን በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ።

ይሁን እንጂ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ዲጂታል የምዝገባ ስርዓት ለአንዳንድ ፓርቲዎች አዲስ በመሆኑ የቴክኖሎጂ ተግዳሮቶች አጋጥመዋል ብለዋል።

የምዝገባ ስርዓቱ ዲጂታል ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶችን ከምርጫ ቦርድ ጋር በመነጋገር እያስገነዘብን ነው” ያሉት አቶ ማሩ፣ ቦርዱ የፓርቲዎችን ጥያቄ ተቀብሎ የምዝገባ ጊዜውን ማራዘሙ የሚበረታታ መሆኑን ገልጸዋል።

የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው፣ ምርጫው ቀዝቅዟል በሚል የሚነሱ ሀሳቦች ከእውነታው የራቁ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የምርጫው ሂደት የቀዘቀዘ የሚመስለው አዲሱ የዲጂታል አሰራር እና የፓርቲዎች ከስርዓቱ ጋር የመላመድ ሂደት ጊዜ ስለወሰደ እንጂ ተሳትፎ ባለመኖሩ እንዳልሆነ አንስተዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review