AMN – የካቲት 14/2018 ዓ.ም
20 ክለቦችን አቅፎ ፣ ሦስት ቡድኖችን በሊጉ አናት ላይ በእኩል ነጥብ ያስቀመጠው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር ከሳምንታት እረፍት በኋላ ሊጀመር ዛሬ ይጀምራል፡፡ ሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ነገሌ አርሲ በእኩል 35 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሊጉን እየመሩት ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት የሊጉ ሁለተኛ ዙር በዋንጫ ፉክክር ብርቱ ትንቅንቅ ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የሊጉ 19 ሳምንታት 190 ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ በእነዚህ ጨዋታዎች የተቆጠሩት አጠቃላይ ግቦች 320 ናቸው። በሊጉ አንድ ጨዋታ በአማካይ 1.68 ጎል ብቻ ይቆጠራል እንደማለት ነው፡፡ በዘንድሮው የሊግ ውድድር በተጋጣሚዎች ላይ ከሌሎች ቡድኖች የበለጠ ግብ በማስመዝገብ ቀዳሚ የሆኑት መሪው ሲዳማ ቡና መቻል ናቸው፡፡ ሁለቱ ቡድኖች እያንዳንዳቸው 24 ግቦችን ተጋጣሚያቸው
ላይ አሳርፈዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እኩል 22 ግቦችን በማስቆጠር ይከተላሉ፡፡

በመጀመሪያው ምእራፍ ከተደረጉ 190 ጨዋታዎች ውስጥ በመሸናነፍ የተጠናቀቁት 110 የሚሆኑት ናቸው። 80 ጨዋታዎች ወይም 42.1 በመቶዎቹ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡ በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ አቻ በመውጣት የሚስተካከለው የለም፡፡ ካደረጋቸው 19 ጨዋታዎች በ12ቱ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል ፡፡ 6ኛ ደረጃ ላይ ያለው አዳማ ከተማ እና በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ወላይታ ዲቻ 10 ጨዋታዎችን አቻ በማጠናቀቅ ይከተላሉ፡፡ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በተለያየ ቦታ ላይ የሚገኙ ሰባት ቡድኖች ደግሞ እያንዳንዳቸው ዘጠኝ ጨዋታዎችን አቻ አጠናቅቀዋል፡፡
በዘንድሮው ውድድር ፋሲል ከነማ ጠንካራውን የመከላከል ብቃት ለተመልካች አሳይቷል። የቡድኑ ግብ ጠባቂ ካሜሮናዊው ሞይስ ፖዋቲ በ 13 ጨዋታዎች ላይ ምንም ግብ አልተቆጠረበትም፡፡ ፋሲልም በ19 ጨዋታዎች 8 ጎሎች ብቻ ነው የተቆጠረበት፡፡ ፋሲል በአማካይ በሁለት ጨዋታ አንድ ጎል እንኳን አይገባበትም እንደማለት ነው። ሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ 10 ግቦችን ብቻ ተቆጥሮባቸው ፋሲልን ይከተላሉ፡፡
በርካታ ግቦችን በመቆጠር ረገድ በበፀሎት ልዑልሰገድ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንደኝነቱን ይዟል፡፡ የ2016 የሊጉ አሸናፊ 24 ግቦች ተቆጥሮበታል፡፡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ግቦች ይቆጠሩበት እንጂ ግብ በማስቆጠር በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ደረጃ ላይ ካለው ሃዋሳ እኩል ነው፡፡ 22 ግቦችን አስቆጥሯል፡፡ ሚዛኒን መጠበቅ ያልቻለው ንግድ ባንክ በተቆጠሩበት ግቦች ምክንያት 14ኛ ላይ ተቀምጧል።

በዘንድሮው ውድድር ውጤት ከራቃቸው የሊጉ ቡድኖች መካከል አርባ ምንጭ ከተማ በቀዳሚነት ይጠቀሳል ፡፡ ባለፈው ዓመት የሊጉ የመጀመሪያ ምእራፍ ሲጠናቀቅ 8ኛ ደረጃ ላይ የነበረው አርባ ምንጭ ፣ ዘንድሮ 20ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ካደረጋቸው 19 ጨዋታዎችም ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ነው፡፡ አዞዎቹ ያገቡት 10 ጎል ብቻ ሲሆን ፣ 12 የግብ እዳም አለባቸው፡፡ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ተአምር ያስፈልጋቸዋል። ከ19 ጨዋታ ወላይታ ዲቻ ሁለት ፣ መቀለ 70 እንደርታ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሦስት ሦስት ጨዋታዎችን ብቻ በማሸነፍ በወራጅ ቀጠናው ላይ ተቀምጠዋል፡፡
ባለፈው አመት የመጀመሪያው ዙር ሲጠናቀቅ የሊጉ መሪ የነበረው እና ዋንጫውን ማሳካት የቻለው ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያው ዙር ማሸነፍ የቻለው አራት ጨዋታዎችን ብቻ ነው፡፡ በደረጃ ሰንጠረዡም 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ለወራጅ ቀጠናው ቀርቧል፡፡
የግብ ድርቅ በታየበት የመጀመሪያው ዙር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የግብ እዳ ያለባችው ቡድኖች 10 ናችው፡፡ የሁለተኛው ዙር ቀጣይ 19 ሳምንታት ዋንጫውን ለማንሳት እና ላለመውረድ በሚደረጉ ትንቅንቆች ይደምቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአልታየህ ኪዳኔ