AMN – የካቲት 14/2018 ዓ/ም
የእብድ ውሻ በሽታ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፍ እጅግ አደገኛ በሽታ ሲሆን በውሻ ንክሻ ይተላለፋል።
በሽታው በRabies ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት ሲሆን ቫይረሱ ወደ ሰውነት ከገባ በኋላ በነርቭ ስርዓት በመጓዝ አንጎልን ይጎዳል።
በየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር አዲስ አስጨንቅ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ በሽታው ከውሻ በተጨማሪ ድመት፣ ቀበሮ፣ ጅብ እና ሌሎች የዱር እንስሳት በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ ብለዋል፡፡
በቫይረሱ ከተያዘ እንስሳ በአፍና አፍንጫ የሚወጣ ፈሳሽ፤ በሰዎች ቁስል ወይም ዓይንና አፍ ሲገባ በበሽታው የመያዝ እድልን ይፈጥራል ብለዋል።
የበሽታው ምልክቶች ከቀናት እስከ ወራት ድረስ ሊዘገዩ እንደሚችሉ የገለጹት ዶ/ር አዲስ፤ መጀመሪያ ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና በተነከሰው የሰውነት ክፍል ላይ ህመም ወይም የመንቀጥቀጥ ሁኔታ ሊታይ ይችላል።

ከዚያ በኋላ ውሃን መፍራት፣ መጨነቅ፣ መናደድ፣ የአእምሮ ልዩነት እና መውደቅ ያሉ ከባድ ምልክቶችም ይታያሉ።
ምልክቶች ከታዩ በኋላ ሕክምና ለማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ስለሚሆን ብዙ ጊዜ ለሞት ይዳርጋል። ነገር ግን ንክሻ ከተፈጠረ በኋላ በፍጥነት ሕክምና በማድረግ ሙሉ በሙሉ ከሽታው መዳን እንደሚቻል ገልፀዋል።
ውሻ ወይም ሌላ እንስሳ ከነከሰ በኋላ ቁስሉን ወዲያውኑ በሳሙናና በብዙ ውሃ ቢያንስ ለ15 ደቂቃ ያህል መታጠብ እንደሚገባም ዶ/ር አዲስ ገልፀዋል።
የተነከሰበት ቦታ ላይ አልኮል ወይም አዮዲን መቀባት የሚደረሰውን አደጋ ለመቀነስ እንደሚቻል ዶ/ር አዲስ ይመከራሉ፤ በተጨማሪ ወደ ጤና ተቋም በአስቸኳይ በመሄድ የRabies ክትባት መርሀ ግብሩን ሙሉ በሙሉ መጨረስ ከበሽታው በፍጥነት ለመፈወስ እንደሚረዳ ዶ/ር አዲስ አብራርተዋል፡፡

በሽታውን ለመከላከል ውሾችን ማስከተብ፣ ያልታወቁ እንስሳትን አለመንካት፣ ህፃናትን ስለ አደጋው ማስተማር እና የእንስሳት ቁጥጥር ስርዓትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል።
የእብድ ውሻ በሽታን መቶ በመቶ መከላከል ቢችልም፤ ምልክት ከታየ በኋላ ግን ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ሕይወትን መታደግ እንንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ማንኛውም የእንስሳ ንክሻ ቀላል ነው ተብሎ መቆጠር የለበትም የሚሉት ዶ/ር አዲስ፤ በአስቸኳይ የሚወሰድ የሕክምና እርምጃ በእብድ ውሻ በሽታ የሚከሰተውን ሞትና ጉዳት መቀነስ እንደሚቻል ዶ/ር አዲስ አስጨንቅ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አስገንዝበዋል።
በበረከት ጌታቸው