ከወር አበባ መዛባት ጀርባ የተሸሸጉ የጤና ምስጢሮች

You are currently viewing ከወር አበባ መዛባት ጀርባ የተሸሸጉ የጤና ምስጢሮች
  • Post category:ጤና

AMN – ሰኔ 16/2018 ዓ.ም

የወር አበባ መዛባት ወይም ከልክ በላይ መፍሰስ ለብዙ ሴቶች የተለመደ ቢመስልም፣ ፈጽሞ ቸል ሊባል የማይገባውና ከጀርባው ከባድ የጤና እክሎችን የያዘ ድብቅ ምልክት ነው።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሚዲካል ኮሌጂ የማህጸንና ጽንስ ሀኪም ዶ/ር ለሚ በላይ፣ የወር አበባ ችግር አለ ለማለት በዋናነት መጠኑን እና የሚመጣበትን ጊዜ እንደ መስፈርት መጠቀም እንደሚቻል ገልጸዋል።

የወር አበባ ከስምንት ቀናትና ከዚያ በላይ የሚቆይ ከሆነ እንዲሁም በቀን ውስጥ ከአምስት በላይ የንጽህና መጠበቂያዎችን መጠቀም የሚያስገድድ የመጠን መብዛት ካጋጠመ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ዶ/ር ለሚ አሳስበዋል።

በአንድ ሰዓት ውስጥ አንድ እና ከዚያ በላይ የንጽህና መጠበቂያ መቀየር ካስፈለገ እና ይህ ሁኔታ በተከታታይ ለሁለት ሰዓታት ከቀጠለ፣ ሁኔታው የፈጣን ማኅፀን ደም መፍሰስ ምልክት ሊሆን ስለሚችል አስቸኳይ ሕክምና ማግኘት ያስፈልጋል።

ያለምንም እርግዝና የወር አበባ ከሦስት ወር በላይ ሙሉ በሙሉ መቅረት ወይም አሜኖሪያ መከሰቱም ሌላው ትኩረት የሚሻ ምልክት መሆኑን ባለሙያው ጠቁመዋል።

ለችግሩ መንስኤ የታይሮይድ ሆርሞን፣ የጉበት እና የኩላሊት በሽታዎችን ጨምሮ የሆርሞን መዛባት ዋነኞቹ መሆናቸውም ገልጸዋል።

እነዚህ እክሎች እንቁላል የመመረት ሂደትን በማስተጓጎል ለፖሊሲስቲክ ኦቫሪያን ሲንድሮም የሚያጋልጡ ሲሆን፣ በማኅፀን ግድግዳ ላይ የሚበቅል ፖሊፕ የተባለ የሥጋ ቁራጭ፣ ማዮማ የተባሉ የማኅፀን እጢዎች እና አንዳንድ ጊዜ የሦስት ወር የእርግዝና መከላከያ መርፌዎች ለችግሩ መከሰት በምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

የችግሩ የአደጋ ደረጃ እንደ ዕድሜ ክልል እንደሚለያይ ባለሙያው አስገንዝበዋል።

ከ15 እስከ 49 ዓመት ባለው የመውለጃ ዕድሜ ክልል ውስጥ መጀመሪያ የሚጠረጠረው ከእርግዝና ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንደ ውርጃ፣ ከማኅፀን ውጭ እርግዝና ወይም ወደ እጢነት የተቀየረ እርግዝና ሲሆኑ፣ እነዚህም በጊዜ ካልታከሙ ለሕይወት ማለፍ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።

ወደ 50 ዓመት በሚጠጋው የማረጥ ዕድሜ ላይ የሚከሰት ተከታታይ መዛባት ደግሞ ከካንሰር ጋር የተያያዙ የእጢ ምልክቶች ሊሆን ስለሚችል ጥልቅ ምርመራ ያስፈልገዋል።

ዶ/ር ለሚ በማጠቃለያ መልዕክታቸው፣ የወር አበባ መዛባት ራሱን የቻለ በሽታ ሳይሆን የሌላ ድብቅ የጤና ችግር ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በመሆኑም ማንኛውም ተከታታይነት ያለው የደም መፍሰስ መዛባት ሲያጋጥም በአቅራቢያ ወደሚገኝ የጤና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራና ሕክምና ማድረግ እንደሚገባ ዶ/ር ለሚ በላይ አስገንዝበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review