ኢትዮጵያን የመጎብኘት ጉጉት

You are currently viewing ኢትዮጵያን የመጎብኘት ጉጉት

ኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ፣ የራሷ ፊደልና ባህል ያላት ሀገር እንደመሆኗ መጠን የኪነ ጥበብ ታሪኳም ከማንነቷና ከጥንታዊነቷ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው። ከዋሻ ስዕል እስከ አብያተ ክርስቲያናት የግድግዳ ድንቅ ስራዎች፣ ከባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች እስከ ዘመናዊው ሲኒማ ድረስ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ የሕዝቧን እምነት፣ ጀግንነትና ማኅበራዊ ሕይወት እየዘከረ እና እያወሳ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል። ይህች ጥንታዊት ሀገር ከድንጋይ ላይ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት እስከ ብራና መጻሕፍት፣ ከቅዱስ ያሬድ ዜማ እስከ ዘመናዊው የኢትዮ-ጃዝ (Ethio-Jazz) ድረስ የዘለቀ ጥልቅ የጥበብ አሻራ አላት። ይህ ጥበብ የሀገሪቱ መልክ፣ ማንነትና ነጻነት መገለጫም ነው። በዚህም ለመላው የጥቁር ሕዝቦች ኩራት መሆን ችላለች።

ኢትዮጵያ ለጥቁር ሕዝቦች ያላት ትርጉም ከድንበር የዘለለ ነው። በቅኝ ግዛት ዘመን የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ሲወድቁ፣ ኢትዮጵያ በነጻነቷ ጸንታ መቆም መቻሏ ለጥቁሮች ሁሉ የኩራትና የተስፋ ብርሃን ሆኖ አገልግሏል። ይህ እውነት ታዋቂው የዲጂታል ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ አይሾው ስፒድ ኢትዮጵያን በጎበኘ ወቅት በገሃድ ታይቷል።

በእርግጥም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት ወጣቱ አሜሪካዊ የዲጂታል ይዘት ፈጣሪ ዳረን ዋትኪንስ (በቅጽል ስሙ አይሾው ስፒድ – IShowSpeed) ወደ ኢትዮጵያ ያደረገው ጉብኝት ታሪካዊ ነበር ማለት ይቻላል። ይህ ጉብኝት ከተለመደው የቱሪስት ጉብኝት ባለፈ፣ የኢትዮጵያን ባህል፣ ታሪክና ዘመናዊ ገጽታ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለጥበብ ሰዎች አዲስ መነቃቃትን ፈጥሯል።

የስፒድን ጉብኝት ተከትሎ በርካታ ተዋንያን፣ ታዋቂ ሙዚቀኞችና የዲጂታል ዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ያላቸውን ጉጉት እየገለጹ ይገኛሉ። በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚኖሩ ጥቁር አሜሪካውያን ኢትዮጵያን የታሪካቸው ምንጭ አድርገው ማየታቸው ለየት ያለ ስሜት ፈጥሮባቸዋል። ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ አንዱ ታዋቂው አሜሪካዊ የራፕ ሙዚቃ ባለሙያ ዲዲጂ (DDG) ነው።

ዲዲጂ (DDG) ማን ነው?

ሙሉ ስሙ ዳሪል ድዌይን ግራንቤሪ ጁኒየር ነው። ዓለም የሚያውቀው ግን ዲዲጂ (DDG) በሚለው የመድረክ ስሙ ነው። ይህ ሰው ታዋቂ አሜሪካዊ ራፐር፣ የዘፈን ግጥም ጸሐፊ እና የዲጂታል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው።

የዘር ሀረጉ ከአፍሪካዊቷ ሀገር ናይጀሪያ የሚመዘዝ ሲሆን፣ የተወለደው በፈረንጆቹ ጥቅምት 10 ቀን 1997 በፖንቲያክ፣ ሚቺጋን ነው። ትምህርቱን በፖንቲያክ አካዳሚ ተከታትሏል። ዳሪል ገና በልጅነቱ በትምህርቱ ጎበዝ የነበረ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከክፍሉ አንደኛ በመሆን አጠናቅቋል።

ከዚያም ወደ ሴንትራል ሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ አምርቶ የነበረ ቢሆንም፣ ወዲያው ወደ ሙዚቃና ዲጂታል ሚዲያ ፊቱን አዞረ። ይህ ውሳኔ ዛሬ ለደረሰበት ስኬት የመሠረት ድንጋይ መሆኑን ይናገራል። የDDG ጉዞ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2014 ቪዲዮዎችን በዩቲዩብ ላይ በመልቀቅ ነበር። መጀመሪያ ላይ ቀልዶችን፣ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን እና ፈተናዎችን በማቅረብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን አፈራ። ሆኖም ግን የልጅነት ሕልሙ ሙዚቃ ነበር።

እ.ኤ.አ. በ2018 በለቀቀው “Givenchy” የተሰኘ ነጠላ ዜማ በዩቲዩብ ከፍተኛ እይታን በማግኘቱ በሙዚቃው ዓለም ትኩረት እንዲስብ አደረገው። በዚህም ከታዋቂው “Epic Records” የሙዚቃ ኩባንያ ጋር ውል ተፈራረመ። በዚህ ሳይገደብ የራሱን የሙዚቃ ተቋም በማቋቋም ወጣት ተሰጥኦዎችን ማበረታታት ጀመረ።

በአሁኑ ዘመን የኪነ-ጥበብ ዓለም በዲጂታል ሚዲያና በባህላዊው የሙዚቃ ኢንዱስትሪ መካከል ያለው መስመር እየቀጠነ መጥቷል። የዚህ ለውጥ ዋነኛ ማሳያ ደግሞ ዳሪል ድዌይን ግራንቤሪ ጁኒየር ወይም በቅጽል ስሙ DDG ነው ይላሉ በርካቶች። ምክንያቱ ደግሞ ከማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ተነስቶ የቢልቦርድ ሰንጠረዦችን እስከመምራት የዘለቀው ጉዞው ለብዙ ወጣቶች አርአያ በመሆኑ ነው።

በሙዚቃ ስራውም፦

ወጣት ነኝ አቅም ያለኝ

ሀብታም እና ጥቁር ነኝ

የስኬት መንገዴን መቀጠል አለብኝ

እናም በፍጹም

ወደ ኋላ አልመለስም… ይላል በጥቁርነቱ የሚኮራውና ለበርካቶች ድምጽ መሆን የቻለው ይኸው ወጣት።

ዳሪል ድዌይን ግራንቤሪ (DDG) ከአንድ ተራ ቪዲዮ ቀራጭነት ተነስቶ ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈ የሙዚቃ ኮከብ ለመሆን የበቃው በጠንካራ ስራውና በፈጠራ ብቃቱ ነው። ወጣቱ ራፐር ለዲጂታል ዘመን ወጣቶች “ሕልምን እውን ለማድረግ ገደብ የለም” የሚል ሕያው ምስክር ነው። ዲዲጂ ለኢትዮጵያና አፍሪካ ልዩ ፍቅር ያለው ወጣት አርቲስት ነው። የናይጀሪያው “ዘ ኔሽን” ጋዜጣ ባሳለፍነው የፈረንጆቹ 2025 እንደዘገበው፣ የራፕ ሙዚቃ ባለሙያው አሜሪካን በመተው ኑሮውን አፍሪካ ለማድረግ ዕቅድ አለው።

የዲዲጂ ኢትዮጵያን የመጎብኘት ዕቅድ

ታዋቂው አሜሪካዊ ዩቲዩበር እና የቀጥታ ስርጭት ባለሙያ ዳረን ዋትኪንስ ጁኒየር ወይም በቅጽል ስሙ አይሾው ስፒድ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት፣ በሀገሪቱ የቱሪዝም እና የገጽታ ግንባታ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ይህ ጉብኝት ኢትዮጵያን ለዓለም ከማስተዋወቅ ባለፈ፣ እንደ ዲዲጂ (DDG) ያሉ ሌሎች ታዋቂ አሜሪካውያን አርቲስቶች ዓይናቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዞሩ አድርጓል።

የአይሾው ስፒድ ቪዲዮዎች ዓለምን ባጥለቀለቁ ማግስት፣ ሌላኛው ዝነኛ አሜሪካዊ ራፐር እና የዩቲዩብ ኮከብ ዳሪል ድዌይን ግራንቤሪ (DDG) ትኩረቱን ወደ ኢትዮጵያ አድርጓል። ዲዲጂ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት፣ የስፒድን ቆይታና የኢትዮጵያውያንን እንግዳ ተቀባይነት ካየ በኋላ ሀገሪቱን ለመጎብኘት ከፍተኛ ጉጉት እንዳደረበት ገልጿል።

ዲዲጂ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣ የገለጸ ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ “የታዋቂ ሰዎች ተከታታይ ጉብኝትን” እየተፈጠረ መሆኑን ያሳያል። የዲዲጂ መምጣት በተለይ ለወጣቱ ትውልድ እና ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ ትልቅ አጋጣሚ ነው። አርቲስቱ ከሙዚቃ ስራው ባለፈ በዩቲዩብ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሉት በመሆኑ፣ የእሱ ጉብኝት ሌላ ተጨማሪ የዓለም አቀፍ ሚዲያ ትኩረትን ይስባል። ይህም ለኢትዮጵያ ቱሪዝምና አዲስ ገጽታ ሌላ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል።

በዓለም አቀፍ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ስመ ጥር የሆነው አሜሪካዊው ራፐር፣ ዩቲዩበር እና ስራ ፈጣሪ ዳሪል ድዌይን ግራንቤሪ (DDG)፣ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ያለውን ጽኑ ፍላጎት በይፋ የማኅበራዊ ትስስር ገጹ መግለጹ በመላው ዓለም በሚኖሩ ጥቁሮችና ትውልደ አፍሪካውያን እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል። ዲዲጂን ከሌሎች አርቲስቶች ለየት የሚያደርገው፣ ስለ ኢትዮጵያ ያለው ፍቅርና የመጎብኘት ፍላጎት ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን፣ ከዚህ ቀደምም በባህሏና በእስክስታዋ እንደሚማረክ በተደጋጋሚ ሲገልጽ የነበረ ሰው መሆኑ ነው።

የዲዲጂ (DDG) የኢትዮጵያ ፍቅር በ“እስክስታ” ተጀምሮ ዛሬ ላይ በታላቅ ጉጉትና በይፋዊ የጉብኝት ተስፋና ፍላጎት ጫፍ ላይ ደርሷል። አይሾው ስፒድ የከፈተው በር፣ ለዲዲጂ እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ከዋክብት ኢትዮጵያን እንደ አዲስ እንዲመለከቷት አድርጓቸዋል። ምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያም እንደ ዲዲጂ ያሉ የጥበብ ሰዎችን በክብር ለመቀበልና የባህልና የዘመናዊነት ጥምረትዋን ለዓለም ለማሳየት ዝግጁ የሆኑ በርካታ መዳረሻዎችን አዘጋጅታለች። በርካታ ተከታዮቹና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉዞውን እንደሚደግፉና ምድረ ቀደምት ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የሚያደርገው ጉዞ ስኬታማ እንዲሆንለት እያበረታቱት ይገኛሉ።

በአጠቃላይ በርካታ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ሰዎች ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ጉጉት እንዳላቸው እየገለጹ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያላት የተፈጥሮ ስጦታ እና ሰው ሠራሽ ሀብት ማለቂያ የለውም። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የተገነቡት ዘመናዊ ፓርኮች፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች ሀገሪቱን ከታሪካዊነቷ ባለፈ ለዘመናዊ ጎብኚዎች ምቹ አድርገዋታል። ጥንታዊ ታሪክ ከዘመናዊ ሥልጣኔ ጋር የተዋሃደባት ሀገር በመሆኗ፣ ኢትዮጵያ የብዙ ጎብኚዎች ቀዳሚ ፍላጎት ሆና ስሟ እንዲነሳ ምክንያት ሆኗል።

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review