AMN ሐምሌ 21/2018

የቤኒን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሪን አሞሪ ብሩኔት፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንስታንት ሰርጌ ቡንዳ እና የሞዛምቢክ የውጭ ጉዳይና ትብብር ሚኒስትር ማሪያ ሚኑኤላ ሉካስ በ49ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገቡ።
በ49ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ የሚሳተፋ የተለያዩ የሕብረቱ አባል ሀገራት የልዑካን ቡድን አባላት ከትናንት ጀምሮ አዲስ አበባ እየገቡ ነው።

የቤኒን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሪን አሞሪ ብሩኔት፣ የኮንጎ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮንስታንት ሰርጌ ቡንዳ እና የሞዛምቢክ የውጭ ጉዳይና ትብብር ሚኒስትር ማሪያ ሚኑኤላ ሉካስ በ49ኛው የሕብረቱ ሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ ለመሳተፍ አዲስ አበባ ገብተዋል።
የሶስቱ ሀገራት ሚኒስትሮች ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አቶ መላኩ በዳዳ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ “የአፍሪካን አጀንዳ 2063 ለማሳካት ዘላቂ የውኃ አቅርቦት እና ደህንነቱ የተጠበቀ የንፅህና አጠባበቅ ስርዓት ማንበር” በሚል መሪ ሀሳብ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ሕብረት ዋና መስሪያ ቤት ይካሄዳል።

የሥራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት በአፍሪካ ሕብረት የ2026 የዓመቱ መሪ ሀሳብ ትግበራና አፈፃፀምን በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ላይ በጥልቀት ይመክራል።
የአፍሪካ ሕብረት ስምምነቶች በቅልጥፍና በሚጸድቁበትና ገቢራዊ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች እንዲሁም በአጀንዳ 2063 ትግበራ ዙሪያ በቀረበው የኮሚቴው ሪፖርት ላይ ይወያያል።