AMN- ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

የቻይና-አፍሪካ ሆስፒታሎች ህብረት የትብብር ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን አጋርነት የበለጠ ያጠናክራል ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ስላሴ ገለጹ፡፡
የቻይና-አፍሪካ ሆስፒታሎች ህብረት የኢንዶስኮፒክ እና የሚኒማል ኢንቬሲቭ ቀዶ-ህክምና የትብብር ፕሮግራም ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት እና የቻይና-አፍሪካ የሮቦቲክ ቀዶ-ህክምና ስልጠና ማዕከል እና የቻይና-አፍሪካ የኢንዶስኮፒክ ቴክኖሎጂ ስልጠና ማዕከል የምርቃ ስነ-ስርዓት ተካሂዷል፡፡

ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ስላሴ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የቻይና-አፍሪካ ሆስፒታሎች ህብረት የትብብር ፕሮግራም በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን አጋርነት የበለጠ ያጠናክራል፡፡
በህክምና ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ማስተዋወቅ የመንግስት ኃላፊነት መሆኑን በመግለፅ ቴክኖሎጂ በጤና ውጤቶች ላይ ያለውን ተጽዕኖ አስረድተዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ ተቋማቸው የኢትዮጵያን የጤና ሪፎርም አጀንዳ ወደፊት ለማስቀጠል በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
የጤና የሰው ኃይል ልማት ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ መሆኑንም ተናግረዋል።

የማሰልጠኛ ማዕከላቱ ለቀጣዩ ትውልድ የኢትዮጵያ የቀዶ ህክምና ባለሙያች ማፍሪያ ሆነው ያገለግላሉ ያሉት ሚኒስትሯ እነዚህ ማዕከላት ለመላው የአፍሪካ አህጉር የእውቀት እና የላቀ አገልግሎት ማዕከል እንደሚሆኑም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ፤ ቻይና እና ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ጠንካራ ትብብር መገንባታቸውን በመግለጽ በጤናው ዘርፍ በሰው ኃይል ልማት ላይ አብረን መስራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።
የረቀቀ የቀዶ ህክምና ማሰልጠኛ ተቋማቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሱዳን፣ ዩጋንዳ፣ ሊቢያ፣ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ ከ 30 በላይ ተሳታፊዎች በመጀመሪያ ዙር ስልጠና መስጠት ጀምረዋል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ እና በቻይና መካከል ያለውን ተቋማዊ ትብብር የሚያጠናክር የመግባቢያ ስምምነት መፈረሙን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
See less