AMN- የካቲት 17/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ እምብርት ላይ የቆመው የአድዋ ድል መታሰቢያ፣ የታሪክ ማህደር ብቻ ሳይሆን የከተማዋ የለውጥ ፋና ወጊ እና የዘመናዊነት መገለጫ ሆኖ ብቅ ብሏል።
የዛሬ 129 ዓመት አባቶቻችንና እናቶቻችን በአድዋ ተራሮች ላይ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል የኩራት አሻራ አኑረዋል።
ዛሬ ደግሞ ያ ታሪካዊ ድል በመሀል አዲስ አበባ በደመቀና ዘመናዊ በሆነ መልኩ “የይቻላል” መንፈስ ተምሳሌት ሆኖ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ እነሆ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል።
የመታሰቢያ ማዕከሉ አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ቀዳሚ ምርጫ እንድትሆን ትልቅ አቅም ፈጥሯል። በውስጡ 2 ሺህ 314 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የፓን አፍሪካን አዳራሽ ይዟል።
አዳራሹ፣ ዘመናዊና ምቹ የመብራት ቅንብር፣ ጥራት ያለው የድምፅ ሥርዓት እና የተሟላ የማቀዝቀዣ ሥርዓት ያለው በመሆኑ ለከፍተኛ ጉባኤዎች ተመራጭ ያደርገዋል። ለረጅም ዓመታት ታጥሮና ተደብቆ የቆየው ይሄው ስፍራ፣ ዛሬ የአራዳን ገጽታ ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል።
የመታሰቢያው ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኩመላ ገብረማሪያም እንደሚሉት፣ አድዋ የተገነባው የከተማዋን ገጽታ ከመለወጥ ባለፈ አሁን ለተጀመረው ሰፊ የኮሪደር ልማት እንደ መነሻና አርአያ በመሆን ነው።

አካባቢው ቀድሞ ከነበረበት ድብቅነት ወጥቶ አሁን ለነዋሪውና ለጎብኚው ክፍት የሆነ ማራኪ የመዝናኛ ስፍራ ሆኗል። ተቋሙ ከታሪክ ማሸጋገር ባለፈ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
በግቢው ውስጥ የሚገኘው አስደናቂ የውሃ ፏፏቴ (ፋውንቴን) በሳምንት ለስድስት ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ ወጣቶች፣ አረጋውያንና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ያለምንም ክፍያ እንዲዝናኑበት እየተደረገ ነው።
ይህም ማዕከሉ የህዝብ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል። አድዋ ድል መታሰቢያ የንግድ እንቅስቃሴውም የታሪክ አካል እንዲሆን አድርጓል። ማዕከሉ፣ 33 የሚጠጉ ሱቆች፡ ባንኮች፣ ሱፐርማርኬቶች እና ቡቲኮችን አካቷል።
የቀድሞውን የአራዳ ትዝታ ለማደስ፣ ለረጅም ጊዜ የታወቀው የባቅላባ ቤት አገልግሎት ወደ ማዕከሉ እንዲገባ ተደርጓል። አድዋ የትላንት የድል አሻራ፣ የዛሬ የልማት መነሻና የነገ የተስፋ ተምሳሌት ነው።
የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የሆነው ይሄው መታሰቢያ፣ አዲስ አበባን በልማትና በቱሪዝም የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ የሚደረገውን ጥረት በግንባር ቀደምትነት እየመራ ይገኛል።
በታምራት ቢሻው