አጥንት ከስክሶ፣ ደምን አፍስሶ ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ የአርበኞች ሚና በታሪክ ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይይዛል። የአርበኛነት መገለጫው በጦር ሜዳዎች ላይ የሚካሄዱ ውጊያዎችን መፈጸም ብቻ ሳይሆን፤ ሀገርን ከድህነት የተላቀቀች እና ለተተኪው ትውልድ የምትመች አድርጎ በጠንካራ መሰረት ላይ መገንባትንም ያካትታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ዘመኑን የዋጀ የአርበኝነት ገድል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ጽሑፍ በጉዳዩ ዙሪያ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን አስተያየት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ሁሉም በተሰማራበት የሥራ መስክ ሀገርን በሀቀኝነትና በታማኝነት ማገልገል ይኖርበታል
የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊት ከሠራው ድንበር ተሻጋሪ ጀብዱዎች መካከል አንዱ በሆነው “የኮንጎ ዘመቻ” ላይ በክቡር ዘበኛነት ተሳትፌአለሁ፡፡ በልዩ ወታደራዊ ብቃትና ዲሲፕሊን በታከለበት አግባብ ተልዕኳችንን በማስፈፀም ረገድ ወሣኝ ሚና ለመጫወት ከቻሉት መካከል አንዱ ነኝ። በየዘመናቱ የሚፈፀሙ የአርበኛነት ታሪኮቻችን ውስጥ ትልቅ አቅም የሚሆነን በልባችን የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ አትመን ማስቀመጣችን ነው፡፡ የጥንት አባቶቻችንና እናቶቻችን የአርበኝነት ታሪክ በደማቁ በደም አሻራ የተከተበ ነው፡፡ በጠላት ባህልና ወግ እንዳንተበተብ፣ በራስ ማንነታችን አሸብርቀን በኩራት ከአንገታችን ቀና ብለን ለመሄድ ምክንያት ሆነውናል፡፡

አርበኛነት ለሀገር እና ሕዝብ በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ መሳተፍን ያካትታል፡፡ እያንዳንዱ ዜጋ በቆመበት ቦታ የሚያደርገው አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሀገርን ትንሳኤ እውን በማድረግ ረገድ እገዛው ትልቅ ነው፡፡ ወቅቱ የሚፈልገው አርበኝነት፤ ሁሉም በተሰማራበት የስራ መስክ ሀገርን በሀቀኝነትና በታማኝነት ማገልገልን ነው፡፡ ይህንንም በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል፡፡
አርበኝነት ማለት ሀገርን በሚያስከብርና በከፍታ ላይ በሚያስቀምጡ ተግባራት ላይ መሳተፍ መቻልን ያመላክታል
ለስልጣኔ መነሾ በሆንባቸው ዘመናት ለዓለም የሚጎበኙ ቅርሶችን በማስተዋወቅ አንድ ብለን የጀመርነውን ስራ አሁንም ማስቀጠል ይጠበቅብናል፡፡ አርበኝነት ማለት ለእኔ “ሀገርን በሚያስከብርና በከፍታ ላይ በሚያስቀምጡ ተግባራት ላይ መሳተፍ መቻልን” ያመላክታል። ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም በርካታ ስራ አቅላይ ተግባራትን ለመከወን የሚቻልበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ከዓለም ጋር እኩል ለመራመድ በምናደርገው ጥረትም መንግስት አምስት ሚሊየን የኮደርስ ሰልጣኞችን በነፃ በማሰልጠን መሰረታዊ እውቀትን ለመሸመት በሚያስችል አግባብ እድሎችን አመቻችቶ ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል፡፡ እንደነዚህ ያሉ እድሎችን በመጠቀምና የራስን ጥረት በማከል ለሀገር አንድ እርምጃ የሚያራምድ ስራ መሰራት ይኖርበታል። ፍላጎቶቻችንን መሬት የወረደ ስራ በመስራትና ለተግባራዊነቱ በመጣር ለሀገር ያለንን ፍቅር በአርበኝነት መንፈስ ማጠናከር ይገባል ባይ ነኝ፡፡

አርበኝነት፡- በተባበረ አቅም ጠንካራ ሀገር መፍጠር መቻል ነው
የጥንት አባቶቻችን እና እናቶቻችን የሀገርን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ረገድ የከፈሉት መስዋዕትነት ትልቅ የአርበኝነት ተግባር ነው። እኛም ይህን መድገም ይጠበቅብናል፡፡ በዚህ ረገድም የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ፣ ውጤቶችም እየተመዘገቡ ነው፡፡
የጋራ የድል ታሪካችንን አንድ ሁለት ብለን ስናነሳ በቅርቡ ከፍፃሜ ያደረስነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሽ ነው፡፡ አርበኝነት ለእኔ የጋራ በሚያደርጉ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ እውቀት ያለው በእውቀቱ በተባበረ አቅም ጠንካራ ሀገር መፍጠር መቻል ነው። ሀገረ መንግስት በተጠናከረ አግባብ ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ሁሉም በተሰማራው የስራ መስክ ውጤታማ ስራ መስራት ይጠበቅበታል።በተለይም ባለጉዳዩን ከማጉላላት አና ባልተገባ ስነ ምግባር ከማስተናገድ ይልቅ ትህትና በተላበሰ አግባብ አገልግሎት መስጠት አንዱ የአርበኝነት መገለጫ ነው። በተለይ ደግሞ ከውጭ ሀገራት በሚደረገው ድጎማ ላይ ከመንጠልጠል ይልቅ በራስ አቅም ችግሮችን ቀርፎ ለመውጣት የሚደረገውን ትኩረት አሁን ላይ በስፋት ይስተዋላል። ታድያ እኔም እንደ አንድ ዜጋ ሀገራችን ከድህነት እንድትላቀቅ የበኩሌን ጥረት እያደረግኩ ነው፤ እሱን አጠናክሬ እቀጥላለሁ፡፡

‘ይሄ ስራ ለነገ ይሁን’ ብሎ የማያሳድር ኢትዮጵያዊ ለእኔ አርበኛ ነው
አርበኛነት ማለት በእኔ አረዳድ ለሀገራችን ያለን መሰጠት፣ ፍቅር፣ መዋደድ እንዲሁም እርስ በእርስ መተሳሰብ የሚለውን ትርጉም ይይዛል፡፡ የአርበኛነት መገለጫዎቹ እጅግ ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ የኛ የኢትዮጵያውያንን የጀግንነት ታሪክ ያወሳን እንደሆነ የዓድዋ ድል የጀግንነት ታሪካችን ነው፡፡ ብርቱ ሃያላንና የሀገር ፍቅር ስሜት ውስጣቸው የሞላ አርበኞች የሚገኙባት ሀገር መሆኗን ከግምት ውስጥ ማስገባት ሳይችል አሰፍስፎ የመጣው ጠላት ውርደትን እንዲከናነብ አድርጎታል፡፡

ይህ ዘመን በመሰረታዊነት በቴክኖሎጂ፣ በኢኮኖሚው፣ በምግብ ራስን መቻልን የሚጠይቅ ነው፡፡ የምዕራባውያንን ደጅ መጥናት እና ከልመና አዙሪት አለመውጣት በራሱ በጦር አውድማ ላይ ከመሸነፍ የተናነሰ አይደለም፡፡ በኛ ዘመን ወቅቱ ከሚፈልገው የአርበኝነት ጀብዱ መካከል የአምራች ኢንዱስትሪውን በመደገፍ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶችን መተካት አንዱ ነው፡፡ ይህ ሲባልም ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች እንዲመረቱ ከማድረግ አንፃር እንደ አዲስ አበባ ከተማ የተጀመሩ እንደ ኢትዮጵያ ታምርት ያሉ መርሃ ግብሮችን በመደገፍ የሀገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ ያስፈልጋል። “ደከመኝ ሰለቸኝ፤ ይሄ ስራ ለነገ ይሁን ብሎ የማያሳድር ኢትዮጵያዊ ለእኔ አርበኛ ነው፡፡
በሄለን ጥላሁን