ሳይንስና ቴክኖሎጂን የብልጽግናችንና የኢኮኖሚ ዕድገታችን ዋና ምሦሶ አድርገናል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing ሳይንስና ቴክኖሎጂን የብልጽግናችንና የኢኮኖሚ ዕድገታችን ዋና ምሦሶ አድርገናል-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN- ሰኔ 13/2018 ዓ.ም

የሀገራችንን ሁለንተናዊ መዋቅራዊ ሽግግር ለማፋጠን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን የብልጽግናችንና የኢኮኖሚ ዕድገታችን ዋና ምሦሶ አድርገናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ለዚህ ስኬትም መንግሥት በቀረጸው የትምህርት ፖሊሲ በመታገዝ ብቃት ያለው፣ የፈጠራ ክሂሎት የተላበሰና ምርታማ የሰው ኃይል ለመገንባት በትጋት እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ ዛሬ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተን የ2018 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎችን ያስመረቅንበት ሥነ ሥርዓት፣ በሳይንስና ፈጠራ የላቀ ዕውቀትን የሰነቁ የለውጥ መሐንዲሶቻችን ወደ አዲስ የሥራና የፈጠራ መስክ የተሻገሩበት አዲስ ምዕራፍ ነው ብለዋል።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የፈጠራ ማዕከላትና የለውጥ ሞተሮች በመሆን ለሀገሪቱ ችግሮች ምላሽ የሚሰጥ ምርምር የማካሄድ እና ለአካባቢው ተስማሚ ቴክኖሎጂዎችን የማልማት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸው፤ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በዚህ ረገድ የጀመረው ስኬታማ ጉዞ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

የተማረ ወጣት ኃይላችን በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ሊያሳየው የሚገባው የፈጠራ ቁርጠኝነት እና የሳይንስ ብስለት፤ በሀገራችን የዲጂታል ሽግግርና የልማት ጉዞ ላይ የተጋረጡ የኋላቀርነት ማነቆዎችን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ የሚያስችል ትልቅ ዐቅም ነው ብለዋል።

መንግሥት ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመራቂ ባለሞያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ያረጋገጡት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለተመራማሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠሩ ረገድ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review