የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ እያዘመነ መሆኑን አስታወቀ

You are currently viewing የአዲስ አበባ ሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የወሳኝ ኩነቶችን ምዝገባ እያዘመነ መሆኑን አስታወቀ

AMN- የካቲት 25/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፣ በከተማዋ የሚከናወኑ የወሳኝ ኩነት ምዝገባዎችን ዓለም አቀፍ አሠራርን በተከተለ መልኩ ለመመዝገብ የሚያስችል የተቀናጀ አሠራር እየተገበረ መሆኑን አስታወቀ።

የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጥጋቡ ሹመይ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል እንደገለጹት፤ ተቋሙ የልደት፣ የጋብቻ፣ የፍቺ፣ የጉዲፈቻና የሞት ኩነቶችን በአግባቡ ለመመዝገብ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ ይገኛል።

ይህንን የምዝገባ ሂደት ውጤታማ ለማድረግም ኤጀንሲው ከ147 የጤና ተቋማት ጋር ለልደት ምዝገባ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከሚገኙ 11 የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምድብ ችሎቶች ጋር ለፍቺና ለጉዲፈቻ ምዝገባዎች የጋራ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

በተጨማሪም ኩነቶች እንደተከሰቱ ወዲያውኑ መመዝገብ የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋት ከትምህርት ቤቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከፖሊስ ጋር በቅርበት እየተሠራ መሆኑን ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።

እንደ አቶ ጥጋቡ ገለጻ፣ የምዝገባ አሠራሩ በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ መሆኑን ገልጸው፤ የመጀመሪያው “በወቅቱ የሚደረግ ምዝገባ”፣ የልደት ኩነት በተከሰተ በ90 ቀናት ውስጥ፣ እንዲሁም ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ጉዲፈቻና ሞት በተከሰቱ በ30 ቀናት ውስጥ የሚከናወን አገልግሎት ነው።

ኩነቱ ከተከሰተ ከአንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የሚደረግ ምዝገባ “በዘገየ ምዝገባ” ሥር የሚመደብ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በላይ የቆዩ ኩነቶች ደግሞ “ጊዜ ገደብ ያለፈበት ምዝገባ” ተብለው እንደሚመዘገቡ ገልጸዋል።

ይህ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለሀገሪቱ የስታቲስቲክስ መረጃ ጥራት፣ ለሕግ ተገቢነትና ለአጠቃላይ አስተዳደራዊ ሥራዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይሁን እንጂ ለሀገራዊ ስታቲስቲክስ ግብዓት የሚውሉት በወቅቱና በዘገየ የምዝገባ ወቅት የተመዘገቡ መረጃዎች ብቻ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review