AMN የካቲት 26/2018
የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ (ESX) የካፒታል ገበያን ለሁሉም ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል “ንዋይ” የተሰኘ የሞባይል ግብይት መተግበሪያ ዛሬ ይፋ አድርጓል።
መተግበሪያው በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ማንኛውም ግለሰብ በሞባይል ስልኩ በመጠቀም በአክሲዮን እና በዕዳ ሰነዶች ግብይት ላይ በቀጥታ እንዲሳተፍ እድል የሚሰጥ ነው።
የኢትዮጵያ የሰነደ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን እስማኤል (ዶ/ር) በመተግበሪያው የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ “ንዋይ” ገበያውን በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እጅ ላይ ተደራሽ ያደርገዋል።
መተግበሪያው ባለሀብቶች በማንኛውም ጊዜና ቦታ ሆነው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ በቀጥታ እንዲሳተፉ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰው የሰነድ ግዢና ሽያጭ ትዕዛዞችን በስልክ ማስተላለፍና መፈጸም እንሚያስችልም ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀና ተህልቁ በበኩላቸው በርካታ ሀገራት ወደዚህ ዓይነት የቴክኖሎጂ ሥርዓት ለመድረስ ረጅም ጊዜ እንደወሰደባቸው አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ ግን ከሌሎች ሀገራት ተሞክሮ በመማር በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘመናዊ የገበያ ሥርዓት መገንባቷን ገልጸዋል።
ይህ ሥርዓት ልዩ የሚያደርገው አካታችነቱ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ በሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ ያሉ ዜጎች የኢንቨስትመንት አካውንት በመክፈት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
መንግስት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው ግልጽና ተገማች የሆኑ ህጎች መውጣታቸው ለዚህ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጉን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥራ አስፈጸሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ ገበያው ሁሉም ዜጋ በአቅሙ ልክ የሚሳተፍበት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
እንደ ቴሌ ብር እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (CBE) መተግበሪያዎች ያስመዘገቡት ስኬት ለ”ንዋይ” ውጤታማነት እንደ ማሳያ እንደሚጠቀስም ገልጸዋል።
መተግበሪያውን በአሁኑ ወቅት በአንድሮይድ (Android) እና በአይኦኤስ (iOS) ስልኮች ላይ ለመጫን ዝግጁ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የካፒታል ገበያ ባለቤት ማድረግ ግብን ለማሳካት እየተሰራ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።