AMN- ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም
አቅርቦት ላይ በትኩረት በመሰራቱ የስጋ ዋጋን ማስተካከል መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ፡፡
የኑሮ ዉድነት ማረጋጋት፣የንግድ ስርዓት መግራትና አዲስ አበባ ታምርት ክላስተር የ2019 የ2ተኛዉ ሩብ ዓመት የጥቅምት ወር ዕቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል።
በመድረኩም የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ ፣የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ፣የ11ንዱም ክፍለ ከተማ ስራ አስፈፃሚዎች እና የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዉበታል።
አቅርቦት ላይ በትኩረት በመሰራቱ የስጋ ዋጋን ማስተካከል ተችሏል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የአዲስ አበባ ከተማ ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ፤የ2019 የ2ተኛዉ ሩብ ዓመት የጥቅምት ወር ዕቅድ አፈፃፀም በተገመገመበት መድረክ ላይ አንስተዋል።
ለማህበረሰቡ ከሚቀርቡት ስጋ ጥራት ጋር በተገናኘም አመርቂ ዉጤት መታየቱን በማንሳት ሸማች ማህበራት አገልግሎታቸዉን ማዘመን ላይም የሚታዩ ስራዎች መሰራታቸዉን ገልፀዋል።
የታዩ ዉጤቶች ተጠናክረዉ እንዲቀጥሉም የደላላን ጣልቃ ገብነት ማስቀረት፤ የሸማች ማህበራት ስጋ ቤቶች ላይ የሚደረገዉ ቁጥጥርም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አንስተዋል።

ህገ ወጥ ንግድን ከመቆጣጠር፣ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች ላይ የምርት አቅርቦት እና መዳረሻዎችን በማስፍፍት ረገድ በ2019 2ተኛ ሩብ ዓመት በጥቅምት ወር ዉስጥ አመርቂ ዉጤት መታየቱን የገለፁት ደግሞ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ናቸዉ።
በቀጣይም በምርት አቅርቦት ላይ በስፋት እንደሚሰራ ገልፀዋል። በግምገማዉ የተነሱትን ጥንካሬዎች ለማስቀጠል እና ክፍተቶች ላይ ደግሞ በትኩረት ለመስራት የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በትባረክ ኢሳያስ