2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አሳታፊና አቃፊ ሆኖ በስኬት ተጠናቋል – ብልፅግና ፓርቲ

You are currently viewing 2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አሳታፊና አቃፊ ሆኖ በስኬት ተጠናቋል – ብልፅግና ፓርቲ

AMN- ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 2ኛው የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ አሳታፊና አቃፊ በሆነ መንገድ በስኬት መጠናቀቁን የብልፅግና ፓርቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዋና ዳይሬክተር ነብዩ ስሁል አስታወቁ።

የጉባኤውን መጠናቀቅ አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት አቶ ነብዩ ስሁል፤ መድረኩ ከ54 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ 1 ሺህ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች፣ ተቋማት እና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ታላቅ አህጉራዊ ክስተት እንደነበር ገልጸዋል።

በጉባኤው ወቅት የብልፅግና ፓርቲ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ የፖለቲካና የድርጅት አቅም ያለው መሆኑ የተረጋገጠበት እንደነበር የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በተለይም በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ እና በማህበራዊ ዘርፎች ያስመዘገበቻቸው ስኬቶችና ባለፉት 9 ወራት የታዩ አበረታች ውጤቶች ለተሳታፊዎች በሰፊው ተሞክሮ ሆነው መቅረባቸውን አስረድተዋል።

ተሳታፊዎቹም የኢትዮጵያ የልማትና የእድገት ተሞክሮ እጅግ ያደገ እና ለአፍሪካ ሀገራት የሚተርፍ መሆኑን መግለጻቸውንም ተናግረዋል።

በአዳራሽ ውይይቶች ብቻ ሳይወሰኑ፤ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽሕፈት ቤት ኤግዚቢሽንና ዶክመንቴሽን ማዕከልን፣ የሐሳብ ጥራት ማሳያ የሆነውን መሶብ የመንግሥት አገልግሎት ማዕከልን፣ እንዲሁም የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክቶችን በአካል ተገኝተው መጎብኘታቸውንም ገልጸዋል።

ጉባኤው ለአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጣይ ትብብር የሚሆን የሦስት ዓመት አደረጃጀት የዘረጋ ሲሆን፤ ይህንንም አደረጃጀት በሰብሳቢነት እንዲመሩ የብልፅግና ፓርቲ የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) መሾማቸውንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የብልፅግና ፓርቲ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ፓርቲዎች ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ የመግባቢያ ስምምነቶችን መፈራረሙ ተጠቅሷል።

በመግለጫው ማጠቃለያም ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ጋር የተያያዙና እስከ እ.ኤ.አ 2040 ሊተገበሩ የሚችሉ አህጉራዊ አጀንዳዎች መቀመጣቸው ጠቅሰው፤ ጉባኤው በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አህጉራዊ መሪዎች፣ ለሚዲያ አካላት፣ ለጸጥታ አካላት እና አጠቃላይ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላሳዩት የላቀ እንግዳ ተቀባይነት ምስጋና ቀርቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review