AMN – ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም
የኢትዮጵያን የእስልምና ታሪክና መንፈሳዊ እሴቶች ለሀገረ መንግሥትና ለሥልጣኔ ግንባታ ማዋል እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነሀ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው በስተላለፉት መልዕክት ዛሬ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የ2ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባዔ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ በመገኘቴ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል።
የነቢዩ ዩሱፍ ታሪክ በቅዱስ ቁርዐን ከሚገኙ ታላላቅ ትምህርቶች አንዱ ነው። የቤተሰብ ፍቅርንና ክህደትን፣ መከራንና ፈተናን፣ በመጨረሻም በእምነትና በፅናት እውነትን ማሸነፍን ያስተምረናል። ኢትዮጵያም በታሪኳ ብዙ ሤራዎችንና መከዳቶችን አልፋለች። የተተበተቡባትን ወጥመዶች ሁሉ በጣጥሳ ወደ ተገባት ክብርና ሥልጣኔ እንደምትመለስ ያለን እምነት ጽኑ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በእስልምና ታሪክ ልዩ ቦታ ያላት ሀገር ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይሚኒትሩ፣ የነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) አሳዳጊ የኡም አይመን፣ የመጀመሪያው ሙአዚን ቢላል፣ የመጀመሪያው ሂጅራ እና የነጃሺ ምድር ናት። አራተኛዋ የሙስሊሞች ቅዱስ ከተማ ተብላ የምትጠራው ሐረር መገኛም ናት። ይህንን ታሪካዊና ባህላዊ ቅርስ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ለቱሪዝምና ለዓለም አቀፍ ግንኙነታችን በሚገባ ልንጠቀምበት ይገባል ብለዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒትሩ አክለውም የመደመር መንግሥት መንፈሳዊነትን እንደ ታላቅ ሀገራዊ ኃይል ይመለከተዋል። ይህንን ኃይል በአግባቡ ከተጠቀምንበት ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት እንችላለን። መንግሥትም የሃይማኖት ተቋማት ጠንካራና ብቁ እንዲሆኑ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ነው ያሉት።
እኛ ለሀገራችን ያልሠራነውን ማንም አይሠራልንም፤ እኛ ያላሳደግናትን ማንም አያሳድግልንም፤ እኛ ሰላሟን ያልጠበቅንላትን ሀገር ማንም አይጠብቅልንም።
“ለሕዝብ እጅግ የሚጠቅሙ ሰዎች፣ እነርሱ በአላህ ዘንድ እጅግ የተወደዱ ናቸው” እንደተባለው የሕዝባችንን ኑሮ፣ ጤና፣ ትምህርትና ሰላም የሚያሻሽል፤ የኢትዮጵያን የመደመር ሥልጣኔ የሚገነባ በጎ ሥራ ሠርተን እንድናልፍ አደራ እላለሁ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።