ብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ድንጋጌን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው – አደም ፋራህ

You are currently viewing ብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ድንጋጌን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ ነው – አደም ፋራህ

AMN-ጥቅምት 28/2019 ዓ.ም

ብልፅግና ፓርቲ የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች ማለትም የአዲስ አበባ ድንጋጌን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ አረጋገጡ።

አቶ አደም ፋራህ በማሕበራዊ ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ በአዲስ አበባ ከተማ “ለዕድገት መምራት፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደ የአፍሪካ መፃኢ ኢኮኖሚ መሀንዲሶች” በሚል መሪ ቃል ሲካሄድ የቆየው የ2026 የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በጉባኤው የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቃት እና ስነ-ምግባር ያላቸው አመራሮች እንዴት መገንባት እንደሚችሉ፣ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን ማጠናከር፣ ያሉንን እምቅ አቅሞ ወደ ድርጁ አቅሞች በመቀየር የአፍሪካ ሀገራትን ብልጽግና ጉዞ ማፋጠን እንዲሁም የፖለቲካ ቃል ኪዳኖችን ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚ እድገት እና የጋራ ብልፅግና መለወጥ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረናል ብለዋል።

በዚሁ አጋጣሚ ብልፅግና ፓርቲ የጉባኤውን ውሳኔዎች ማለትም “የአዲስ አበባ ድንጋጌ”ን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን ለማረጋገጥ እወዳለሁ ሲሉ ገልጸዋል።

የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ (APPI) ጽህፈት ቤት አዲስ አበባ ላይ እንዲከፈት እንዲሁም ጽ/ቤቱን የሚመራው የዋና ጸሐፊነት ኃላፊነት ለብልፅግና ፓርቲ ተወካይ እንዲሰጥ በጉባኤው የተደረሰውን ውሳኔ በደስታ እንቀበላለን ብለዋል።

አቶ አደም ተሳታፊ ፓርቲዎች ለሰጡን ለዚህ ትልቅ እምነት እያመሰገንን፣ የተጣለብንን ኃላፊነት በትጋት እና በፅናት እንወጣለን ሲሉ ገልጸዋል።

የአፍሪካ የፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር፣ የልምድ ልውውጥ እና የአቅም ግንባታ ማዕከል እንዲሆን በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ነው የጠቀሱት።

በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ(ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ከአፍሪካ አመራር ልህቀት አካደሚ (AFLEX) ጋር በመተባበር የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን አቅም ለማጎልበት፣ የአመራር ብቃትን ከዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እና ከኢኮኖሚ ብልጽግና ተግባራዊ ኃላፊነቶች ጋር ለማጣጣም በትኩረት እንሰራለን ብለዋል።

ለአፍሪካ አስተዳደር ማዕከል፣ ለተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለአፍሪካ ህብረት፣ ለአስተባባሪዎች እና ይህ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የበጎ ፈቃደኞች ምስጋና አቅርበዋል።

አቶ አደም በመልዕክታቸው ፣ በመደመር እሳቤ በመመራት፣ ልዩ ልዩ አቅሞቻችንን ወደ ጋራ ስኬት እንድንቀየር እንዲሁም በአዲስ አበባ ጉባዔ የገባነውን ቃል ኪዳን በተግባር ወደ ዘላቂ የሕዝቦቻችን ጥቅም እንድንለውጥ አደራ እላለሁ ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review