AMN – የካቲት 30/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተተገበሩ በርካታ የልማት ስራዎች የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየራቸዉም በላይ የከተሜነት ዕሳቤን እና የነዋሪዎችን የአኗኗር ዘይቤ በመቀየር ላይ ይገኛሉ፡፡
በተለይ በኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት የተከናወኑ በርካታ የልማት ሥራዎች መዲናዋ ለነዋሪዎች ምቹ፥ ለቱሪስቶች ሳቢ እና ማራኪ እንድትሆን አስችለዋታል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በአውራ ጎዳናዎች ላይ በዘፈቀደ የሚጣሉ ደረቅ ቆሻሻዎች እምብዛም አይታዩም፤ ምክንያቱም በየመንገዱ ግርጌ በተቀመጡ የደረቅ ቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች ሶፍትን ጨምሮ ሌሎች ደረቅ ቆሻሻዎችን ማስወገድ የዘመናዊነት መገለጫ መሆን ስለቻለ፡፡
ዋና ዋና መንገዶችን ጨምሮ በየስርቻዉ መጸዳዳት፥ ወደመንገድ ፍሳሽ ማስወገጃ እና ወደ ወንዞች ፍሳሽ ቆሻሻዎችን መልቀቅ ማለት አካባቢን መበከል፥ የመዲናዋን ገጽታ ማበላሸት እና የማኅበረሰቡን ጤና መጉዳት መሆኑን አብዛኛዉ ነዋሪ ተረድቶታል፡፡

አዲስ አበባ ላይ ከአሁን በፊት እንደነበረው ተሽከርካሪና እግረኛ እየተጋፉ የሚሔዱበት፤ የሰው ሕይወት በቀላሉ የሚያልፍበት እና የአካል ጉዳት የሚደርስበት ሁኔታ በእጅጉ ተሸሽሏል፡፡
በወንዝና ኮሪደር ልማቱ ዘመናዊ የተሽከርካሪ፤ የእግረኛ እና የብስክሌት መንገዶች በመገንባታቸዉ ማኅበረሰቡ በተፈቀደለት መንገድ ብቻ በነጻነት ያለ ስጋት እንዲንቀሳቀስ አስችሎታል፡፡
መንገዶቹ በተለይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ሲደርሱ የነበሩ ጉዳቶችንና እንግልቶችን በእጅጉ ቀንሰዋል፡፡ ለማረፊያነት የሚያገለግሉ አግዳሚ መቀመጫዎችም በየመንገዱ ተመቻችተዋል፡፡
በየአካባቢዉ የተገነቡ የሕጻናት መጫወቻዎች፤ የስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራዎች፤ ፓርኮችና የመዝናኛ ስፍራዎች መዲናዋን ይበልጥ ያዘመኑ መሠረተ ልማቶች ሆነዋል፡፡
አዲስ አበባ ላይ በዘመናዊ መብራቶች እና በሙዚቃ ታጅበዉ የሚደንሱ ዉሃዎችን መመልከትም ከአሁን ቀደም ያልነበረ የልማቱ ትሩፋት ነዉ፡፡

እንደ ሸረሪት ድር የተወሳሰቡ የኤሌትሪክ እና የቴሌኮም ገመዶች ከመሬት በታች ተቀብረዉ አዲስ እይታን ፈጥተዋል፡፡ የደኅንነት ካሜራዎችም በየቦታዉ ተተክለዉ የወንጀል ስጋቶችን ቀንሰዋል፡፡
ተሽከርካሪዎች በዘፈቀደ በየመንገድ ዳሩ የሚቆሙበት፤ መንገድ የሚያጣብቡበት እና የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታም ተቀይሯል፡፡
ለዚህ ነው የመዲናዋ ተጨማሪ ድምቀት የሆነውን ከዑራኤል – ቦሌ መድኃኔዓለም እስከ ቦሌ ቪአይፒ (VIP) ተርሚናል የሚያገናኘውን የኮሪደር ልማት መርቀዉ ሥራ ያስጀመሩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በከተማዋ እየተከናወኑ የሚገኙ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ መሠረተ ልማቶች መዲናዋን ብቻ ሳይሆን የነዋሪዉን የአኗኗር ዘይቤ የቀየሩ መሆናቸዉን የገለጹት፡፡
አብዛኛዉ የመዲናዋ አካባቢዎች ጽዱ እና ለመኖር እና ለምሽት ንግድ እንቅስቃሴ ምቹ ከመሆን አልፈዉ የቱሪስቶችን ቀልብ እስከመሳብ ደርሰዋል፡፡
አዲስ አበባ በተጀመረዉ ልማት ከጨለማ ተላቃ በብርሃን ደምቃለች ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶችም በተገኘዉ ለዉጥ መደነቃቸዉ ገልጸዋል፡፡
አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ አበባ ለማድረግ የተጀመረው ሥራ አሁንም የመዲናዋን ነዋሪዎች እና ባለሃብቶችን በማሳተፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በወንድማገኝ አሰፋ