AMN-መጋቢት 01/2018 ዓ.ም
የከተማዋን ገጽታ የቀየረው የኮሪደር ልማት ለአነስተኛ ቢዝነሶች አዲስ ዕድልና ዘመናዊ የንግድ ድባብ መፍጠሩን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ስራ አነስተኛ ቢዝነሶችን የሚያዳክም ሳይሆን፣ ይበልጥ ዘመናዊ፣ ለስራ እና ለሸማቹ ሳቢ በሆነ መንገድ መልሶ በመገንባት የተሰራም ጭምር ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ እስከ አሁን በተሰራው 5 ሺህ 490 ያህል አዳዲስ ንግድ ሱቆችን በመገንባት፣ ነባሮቹንም ከመንገድ setback ወደ ኋላ በመሳብ እንደገና በአዲስ መልክ እንዲገነቡ ተደርገዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 2 ሺህ 800 ያህሉ እንደ አዲስ የተገነቡ፣ ቀሪዎቹ 2 ሺህ 690 ደግሞ ከመንገድ setback ወደ ኋላ በመሳብ እንደገና በነበሩበት ቦታ በአዲስ መልክ ደረጃቸውን በማሻሻል የተገነቡ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ከንቲባዋ አክለውም ከዚህ ውስጥ 55 በመቶ የሚሆነው ግንባታ በባለቤቶቹ የተከናወነ ሲሆን ቀሪውን በቀበሌ እና በቤቶች ኮርፓሬሽን ውስጥ ሲነግዱ ለነበሩ መንግስት ገንብቶ ለልማት ተነሺዎች ያስረከባቸው እንደሆነም ገልፀዋል።

መሬት ለመውሰድ ፍቃደኛ የሆኑትንም በአክሲዮን ተደራጅተው እንዲገነቡ ከተማ አስተዳደሩ እየደገፈም ነው ብለዋል። በመሆኑም ከተማዋን ለንግድ ስራ ቀላል፣ ይበልጥ ሳቢና ምቹ አደረግናት እንጂ የቢዝነስ እንቅስቃሴው እንዲዳከም አልተደረገም ሲሉም አፅንኦት ሰጥተዋል።
በሌሎቹ ኮሪደሮች እንደተደረገው ሁሉ ትላንት ማምሻውን በይፋ ክፍት የተደረገው የድል ፕላዛ እና የቁርጡሚ ወንዝ ዳርቻ የልማት ተነሺዎችን አስተናግደንበታል።
በመሆኑም ቀደም ሲል ከቦሌ አትላስ እስከ ብራስ መንገድ በኮሪደር ልማቱ ምክንያት ተነስተው የነበሩ የንግድ ተቋማት፣ አሁን በዚሁ ፕላዛ ውስጥ ስራቸውን በስኬት ጀምረዋል ሲሉ መልዕክታቸውን በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አጋርተዋል።