AMN – ሰኔ 9/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ከሦስት ሺህ በላይ የሚሆኑ ሕፃናትን ከጎዳና በማንሳት ወደ ቤተሰቦቻቸው የመመለስና ወደ ሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት የማስገባት ሥራ መሠራቱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ በአፍሪካ ለ36ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ35ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአፍሪካ ሕፃናት ቀን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፤ በከተማዋ ሕፃናትን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ የልማት ሥራዎች በሰፊው መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ዘንድሮ የሚከበረው የአፍሪካ ሕፃናት ቀንም «ደኅንነቱና ንጽሕናው የተጠበቀ አካባቢ ለሁሉም ሕፃናት» በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ መርኃ-ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
የበዓሉን አከባበር በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት ኃላፊዋ ፤ ሕፃናት የተሳተፉበት የአካባቢ ጽዳት መርኃ-ግብር ፣ የግንዛቤ ፈጠራ ንቅናቄ እና የታዳጊ ሴቶች የንጽሕና መጠበቂያ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመዋል።

ሰኔ 13 ቀን ሕፃናት የሚታደሙበት፣ እንዲሁም ተሰጥኦና ችሎታቸውን በሰፊው የሚያሳዩበት ልዩ መርሐግብር እንደሚከናወንና ይህም የበዓሉ አንዱ አካል መሆኑን አመላክተዋል።
ወ/ሮ ቆንጂት አክለውም ፣ በከተማዋ የቀዳማይ ልጅነት ልማትን ጨምሮ የትምህርት ቤት ምገባ፣ የሕፃናት ማቆያና የመጫወቻ ሥፍራዎች ግንባታን ያካተቱ በርካታ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ለሕፃናት ዘላቂ ደኅንነት መረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውንና ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።
በቤተልሔም አየነው