AMN – መጋቢት 03/2018 ዓ.ም
በደብሊው ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ይፋ የተደረገው የ2026 የአፍሪካ የሆቴል ሰንሰለት ልማት እንቅስቃሴ (Hotel Chain Development Pipelines in Africa) ሪፖርት መሠረት፣ ኢትዮጵያ በሆቴል ልማት ዘርፍ ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር እያሳየች ነው፡፡
ሀገሪቱ ከታቀዱ ፕሮጀክቶች ውስጥ ወደ 80 በመቶ የሚጠጉትን ወደ ግንባታ በመቀየር የምሥራቅ አፍሪካ የቱሪዝም መዳረሻነቷን የሚያጠናክር አዲስ ፋና ወጊ የታሪክ ምዕራፍ እየጻፈች ትገኛለች።
በዚህም ሀገሪቱ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆቴል ልማት ገበያ ካላቸው ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች ብሏል ሪፖርቱ። በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ ላይ የታየው ከፍተኛ መነቃቃት እና የፍላጎት መጨመር፣ አገሪቱን በዘርፉ ቀዳሚ ተመራጭ እያደረጋት ይገኛል።

ለዚህ ስኬታማ ጉዞ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ ዐበይት ነጥቦች መካከል ከተማዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗ፣ የከተማዋ ውበትና የኮሪደር ልማት መስፋፋት እንደዋነኛ ነጥቦች በሪፖርቱ ተገልጸዋል፡፡ ብዙ ሀገራት ሆቴሎችን ለመገንባት ቢያቅዱም፣ ኢትዮጵያ ግን ዕቅዶቿን በተግባር ወደ ግንባታ በመቀየር ረገድ እጅግ ስኬታማ ሆናለች ብሏል ሪፖርቱ።
ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ በአሕጉሪቱ ከፍተኛው የግንባታ ተዋጽዖ የታየባቸው ሀገራት ሆነዋል፤ ይህም የሚያሳየው በአጭር እና በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ አዳዲስ የሆቴል አቅርቦቶች በብዛት የሚጠበቁት በእነዚህ ሀገራት መሆኑን የአፍሪካ የቱሪዝም እና የጉዞ መረጃ ምንጭ የተሰኘ ድረ ገጽ ያትታል፡፡
ምንም እንኳን ሰሜን አፍሪካ በአጠቃላይ በሆቴል ክፍሎች ብዛት የበላይነቱን ቢይዝም፣ ምሥራቅ አፍሪካ ግን ፕሮጀክቶችን በመተግበር፣ ወደ ማጠናቀቂያው ደረጃ በማድረስ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ክፍት በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደም መሆኑን የዘገበው ቮያገርስ አፍሪክ/VoyagersAfriq/ ድረ ገጽ ነው፡፡
በቶለሳ መብራቴ