AMN መጋቢት 3 ቀን 2018ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የግብር ስወራን ለመከላከልና የንግድ ሥርዓቱን ፍትሀዊነት ለማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በተከናወነ የተጠናና ድንገተኛ ኦፕሬሽን በ8 በምንጣፍ የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት ሲፈጽሙ የተገኙ 8 ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር ማዋሉን አሳወቀ።
ቢሮው መጋቢት 3 ቀን 2018ዓ.ም ያካሄደው የኦፕሬሽን ተግባር በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በወለል ምንጣፍ ላይ ተሰማርተው በሕግ የተጣለባቸውን የደረሰኝ አጠቃቀም ግዴታ ባለመወጣት ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ በተያዙ ነጋዴዎች ላይ መሆኑን አሳውቋል።
በዚህም ከድርጊቱ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው የንግድ ስራዎቹ ባለቤቶችና ሽያጩን ያለደረሰኝ ሲያከናውኑ የነበሩ ሰራተኞች የመንግስትን ግብር ለመሰወር ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ ተገኝተው በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን አሳውቋል፡፡
ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ማካሄዱን የተገለፀ ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች የመንግሰትን ጥቅም ለማሳጣት ከታክስ አስተዳደር አዋጅ በተፃረረ መልኩ ያለደረሰኝ ሽያጭ በመፈፀም ወንጀል ተጠርጥረው በአሁኑ ወቅት ጉዳያቸው በፖሊስ ተይዞ ለፍርድ የሚቀርቡ ይሆናል ብሏል፡፡

በቀጣይ ቀናትም ቢሮው የኦፕሬሽን ተግባሩን በሌሎችም ዘርፎች አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ያሳወቀ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ ግብይቶችን በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅም ህብረተሰቡም በ7075 ነፃ የስልክ መስመር በመጠቀም መሰል ወንጀሎችን እንዲያጋልጥ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ቢሮው ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ በጎማ፣ በኤሌክትሮኒክስና በኮንስትራክሽ፣ በስጋ ቤት፣ በግንባታ ዕቃዎች እንዲሁም በሱፍ ልብስ ንግድ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ባካሄደው ኦፕሬሽን በድምሩ 74 ተጠርጣሪዎች ያለደረሰኝ ሽያጭ ሲፈፅሙ እጅ ከፍንጅ በመያዝ በህግ ቁጥጥር ስር ከማዋሉ ባሻገር በኢንቨስቲጌሽን ኦዲት ዳግም ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
በመሆኑን የንግዱ ማህበረሰብ በደረሰኝ ብቻ ግብይት በመፈፀም ከመሰል የህግ ተጠያቂነት እራሱን እንዲጠብቅ ቢሮው ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አሳስቧል፡፡