AMN-ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም
በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት በዜጎች እንቅስቃሴና በኢኮኖሚው ላይ ጫና እንዳያሳድር በአዲስ አበባ ከተማ የተቋቋመው ግብረ-ኃይል፣ ባለፈው አንድ ወር ያከናወነውን የክትትልና ቁጥጥር ስራ ግምገማ ይፋ አድርጓል።
በግምገማ መድረኩ ላይ እንደተገለጸው፣ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ከ37 ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ ለከተማዋ መቅረቡ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ባለፈው አንድ ወር በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገ የክትትልና የቁጥጥር ስራ ለከተማዋ የሚመደበው ነዳጅ በፍትሃዊነት እንዲሰራጭ በመደረጉ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፣ በቁጥጥር ስራው ወቅት በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው የተገኙ 256 አካላት ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።
እርምጃ የተወሰደባቸው አካላትም አመራሮችን፣ የጸጥታ አካላትን፣ የመንግስት ሰራተኞችንና የማደያ ሰራተኞችን ያካተተ መሆኑንም የቢሮ ሀላፊዋ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በህገ-ወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ 59,052 ሊትር ናፍጣ እና 7,340 ሊትር ቤንዚን በቁጥጥር ስር መዋሉን ኃላፊዋ አክለው ተናግረዋል፡፡
በማደያዎች የሚታዩ ረጅም ሰልፎች፣ የማደያ ሰራተኞችና ተራስከባሪዎች የስነ-ምግባር ጉድለት እንዲሁም በሀሰተኛ መታወቂያ ነዳጅ ለመቅዳት የሚደረጉ ሙከራዎች ለስራው እንቅፋት መሆናቸውም ተመላክቷል።
ነዳጁ በአግባቡና በፍትሃዊነት እንዲሰራጭ የ24 ሰዓት የተቀናጀ ቁጥጥር ሲደረግ መቆየቱነቱን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ምክትል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር እርዚቅ ኢሳ ናቸው፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከንግድ ቢሮ እውቅና ውጭ በራሳቸው ደብዳቤ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸው በማደያ ባለቤቶች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመዋል።
በቀጣይም ነዳጅ ማደያዎች ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ በሚወርድ መመሪያ መሰረት ብቻ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው አካላት ማቅረብ እንዳለባቸው አቶ ጃንጥራር አባይ አሳስበዋል።
ፖሊስና የጸጥታ አካላት የፎርጅድ መታወቂያዎችን በመቆጣጠርና ህግን በማስከበር ረገድ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የገለጹት ምክትል ከንቲባው፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችም ስርጭቱ ፍትሃዊ እንዲሆን የተቀናጀ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በአስማረ መኮንን