መጋቢት 4/2018
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማላቅ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በ12 ኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር አንደኛ ደረጃ የዋንጫ ተሸላሚ መሆኑ ይታወሳል።
በዛሬው እለትም የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ታዬ አፅቀ ሥላሴ የአየር መንገዱን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሀገር ምልክት የሆነ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ ለሀገር እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውና የአንደኛ ደረጃ ጥራት ሽልማቱ የሚገባው መሆኑን በተግባር እያስመሰከረ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያንና አፍሪካን ከዓለም በማስተሳሰር ሚናው የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፥ የተቋሙ የሰው ኃይል ጥንካሬ እና የስራ ባህል ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑን ጠቁመዋል።
ተቋሙ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማላቅ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፥ አየር መንገዱ ዓለም አቀፋዊና የሀገር ውስጥ መዳረሻዎቹን እያሰፋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በየጊዜው የአገልግሎት አሰጣጡን እያሻሻለ እንደሚገኝ በማንሳት፥ በዚህም በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ሽልማቶችን ያገኘ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
በቀጣይም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቱን ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡