በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ ቁጥር ያላቸው የክርስትና እና እስልምና እምነት ተከታዮች እንደየ ዕምነታቸው በፆምና በፀሎት ወደ ፈጣሪ ልመናቸውን የሚያቀርቡበት ወቅት ላይ ይገኛሉ። ይህንንም አጋጣሚ መነሻ በማድረግ “በአጿማት ወቅት ተግባራዊ የሚደረጉ እሴቶችን ለሀገር በሚበጅ መልኩ እንዴት ማጠንከር ይቻላል?” በሚለው ዙሪያ የሚከተለውን ጽሑፍ አጠናቅረናል፡፡
መላከታቦር መምህር ኢያሱ ሲሳይ ይባላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በአያት ደብረ ሰላም ዋሻ ቅዱስ ሚካኤል እና በአቡነሃራ ድንግል ማርያም ገዳም አስተዳዳሪ ናቸው፡፡ “አንድ አማኝ ፆም በመፆሙ የሚያገኛቸው ስጋዊ ብሎም መንፈሳዊ ጥቅሞች ምን ምን ናቸው?” ብለን ላነሳንላቸው ጥያቄ በሰጡን ምላሽ፤ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ፆም መፆም ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ ነገር ስለመሆኑ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የሰው ልጅ ከፈጣሪው ዘንድ እንዲሆንለት የሚፈልገውን ጉዳይ በፆምና በፀሎት ይጠይቃል፡፡ አሁን ያለንበት የአብይ ፆምም ታላቁ ጾም በመባል ይታወቃል። እራስን በማዋረድና ዝቅ በማድረግ ልመናና ፀሎትን ለፈጣሪ የምናደርስበት ወቅት ነው” በማለት አብራርተዋል፡፡
እንደ መላከታቦር መምህር ኢያሱ ገለፃ፤ አንድ አማኝ ፆም ለመፆም ሲያስብ በቅድሚያ ከጥላቻ እና ከቂም እራሱን አርቆ መሆን አለበት፡፡ ኃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ አንድ ሰው መፆም ከቻለ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከት፣ ጤናን ብሎም ሰላምን እንዲያገኝ ያደርገዋል። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰባቱ አፅዋማት መካከል አብይ ፆም (ፆመ ሁዳዴ) አንዱ ነው፡፡ እድሜው ለመፆም የደረሰ ሁሉ እየፆመ፣ እየፀለየ፣ እያስቀደሰ በረከት የሚያገኝበት እንዲሁም ስለ ሀገራችን ሰላም፣ ፍቅር እና አንድነት እንዲሰፍን ለፈጣሪ የሚጠይቅበት ነው፡፡ የተቸገሩትም ሁሉ መልካም ነገር የሚያገኙበት ታላቅ በረከት ነው፡፡
ፆም ሲፆም ህዝበ ክርስቲያኑ ምሳሌ ሊያደርገው የሚገባው ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ከቆመ ሳይቀመጥ፤ ከዘረጋ ሳያጥፍ በገዳመ ቆሮንቶስ የተፈተነበት ነው፡፡ ከዚያም ፈተናውን አልፎ ለሰው ልጆች ሁሉ ተቃራኒ ሃሳብ የሚያመጣውን ሰይጣንን በፆም ድል የነሳበት መልካም ተምሳሌታችን ነው፡፡
በፆም ወቅት የሚታዩ ወይም የሚተገበሩ እሴቶች ፋይዳቸውን በተመለከተ መላከታቦር መምህር ኢያሱ ሲያስረዱ፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደተናገረው “ከወዴት እንደሆንክ አስብ” የሚለውን የት እንደሆንን የምናስብበት፣ ራሳችንን የምናይበት እንዲሁም ክርስትናችንንም ከምንጊዜውም በላይ ተግባራዊ የምናደርግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የመልካም እሴቶች ባለቤት መሆናችንን ተከትሎ ክፉዎች ሁሉ ደግ የሚሆኑበት፤ መጥፎ አስተሳሰብ ያላቸው መልካም ነገርን የሚያስቡበት ራሳቸውን የሚገዙበት ታላቅ ፆም ነው። በተለይ ደግሞ ምዕመኑ በአሁን ሰዓት የተቸገረን የሚረዳበት ጊዜ ነው፡፡
በተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት (ዩኒቨርሲቲዎች) የሚገኙ ተማሪዎችም ቁርሳቸውን ለነዲያን የሚሰጡበት ከዚያም አልፎ ተርፎ አልባሳትንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ጭምር ይሰጣሉ። ይህን መሰሉ ተግባር አንዱ የኢየሱስ ክርስቶስ ተምሳሌትነትን የሚያሳይ ተግባር ነው፡፡ የተቸገረውን መርዳት፤ ለራበው በማብላት ለጠማው በማጠጣት ለታረዘው ደግሞ በማልበስ መልካምነት የሚንፀባረቅበት የፆም እሴቶቻችን ናቸውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኡዝታዝ አቡበከር አህመድ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ ልዩ አማካሪ በበኩላቸው እንዳስረዱት፤ “ፆም ከእስልምና መሠረታዊ ድንጋጌዎች ብሎም መመሪያዎች መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው፡፡ ነብዩ ሰ.ዐ.ወ ‘እናንተ ያመናችሁ ሁሉ ባለፉት ህዝቦች ላይ ፆም ግዴታ እንደተደረገው ሁሉ በእናንተም ላይ ተደረገ’ ተብሎ በቅዱስ ቁርዓን ላይ ተገልፆአል፡፡ አማኝ የሆነ ሰው አቅሙ የሚችል ጤነኛ የሆነ ሰው መፆም ግዴታው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡”
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የፆም እሴቶች የሆኑት እንደ አብሮነት፣ መተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ማዘን፣ መልካም ስብዕና እና ርህራሄ ማሳየት፣እርስ በእርስ መደጋገፍ፤ ያለው ለሌለው የማካፈልና የመረዳዳት እሴት በረመዳን ወር ፍንትው ብሎ ይታያል፡፡ በተለይም ካለን ነገር ላይ ለሌላቸው የማካፈልና ፍቅራችንን ያለልዩነት በተግባር ማሳየት የቆዩ እሴቶቻችን ናቸውም” ሲሉ ኡዝታዝ አቡበከር ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባና አካባቢው ቀጠና ዋና ፀሐፊ መጋቢ በለጠ ኃጃሎ እንዳስረዱት ደግሞ፤ “በፆም ወቅት የሰው ልጅ ከመጥፎ ነገሮች የሚቆጠብበት ሃጥያትን የሚፀየፍበት ጊዜ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው ሃጥያትን ፈፅማ የምትፀየፍ ነፍስ እጅግ የተባረከች እንደሆነች ተገልጿል፡፡ በተለይ ወጣቱ እራሱን በዘመን አመጣሽ ግርግር ሳይዋጥ ከተለያዩ ነገሮች በመቆጠብ መልካም ሥነ ምግባርን ይላበሳል፡፡ መልካም ስብዕናን የያዘ ወጣት ለቤተሰቦቹ፣ ለቅርብ ወዳጆቹ እንዲሁም ለሀገር ትልቅ በረከት ነው። ቀጣይ ለሚመጣው ትውልድም ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላልም ብለዋል፡፡
በፆም ወቅት ያሉ እሴቶች ፋይዳቸውን በተመለከተ መጋቢ በለጠ እንደገለፁት፤ እርስ በእርስ ይቅር የመባባያ ጊዜ ነው፡፡ የተጣሉ የሚታረቁበት ሰላማዊ መንፈስ የሚነግስበት የፆም ወቅት ነው፡፡ “ቂም ይዞ ፀሎት ሳል ይዞ ስርቆት” አይቻልምና ሰዎች ከጥላቻ ወደ መግባባት ወደ እርቅ ወደ አንድነት የምንመጣበት የተባረከ የፆም ወቅት ጭምር ነው። አንድ ምዕመን በፆም ወቅት መቆጠብ ያለበት ከእህል ብቻ ሳይሆን አይኑ፣ አፉ፣ ጆሮው እንዲሁም መላ ህዋሳቶቹ ጭምር እንዲፆሙ ያዛል፡፡ አፍ መጥፎ ነገር ከመናገር አይንም የማይገባ ነገር ከማየት እግርም ወደ አልተገባ ስፍራ ከመሄድ የተከለከለ እንዲሆን በተለያዩ መንፈሳዊ ትምህርቶች አማካኝነት ይነገራል፡፡ ይቅር መባባል አንዱ ከፆም የምናገኘው እሴት መሆኑን ተከትሎ በእግዚአብሔር አምሳያ የተፈጠረን ፍጡር መውደድ ያለንን ፍቅር ማሳየት ይቅር ማለት አንዱ አምላካችንን ስለመውደዳችን የሚያሳየን አስተምሮ ነውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኡዝታዝ አቡበከር አክለውም፤ በፆም ወቅት የሚገኙ እሴቶችን ስናይ እንደ ግለሰብ ብሎም እንደ ሀገር ፋይዳው እጅግ የላቀ ያደርገዋል፡፡ ከምንም በላይ ግን የሰው ልጅ ፆም እንዲፈፅም የታዘዘውን መከወኑ መለኮታዊ መመሪያን ተግባራዊ ማድረግ እና ለፈጣሪ ታዛዥነቱን ነው የሚያሳየው፡፡ የሰው ልጅ በፍቃደኛነት በራሱ ላይ ገደብ ይጥላል ወይንም እቀባ ያደርጋል፡፡ ፈጣሪ ከከለከለው ነገር እራሱን በመከልከል በመተው በሌላ ጊዜ የተፈቀዱ እና መልካም የሆኑ ነገሮችን ከሚበላው ብሎም ከሚጠጣው ለፈጣሪ ክብር ሲል በተወሰነ ገደብ ውስጥ ያሳልፋል፡፡ ከብዙ ነገራቶች ራሱን ይገድባል፡፡ ይህም ታዛዥነት ወደ መንፈሳዊ ልዕልና ለመሸጋገር መንፈሳዊ ማንነቱን ለማጠናከር መሠረታዊ ነገር ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡
በመፆም ውስጥ የሚገኙ እሴቶችን አንድ በአንድ መከወን መቻል የሰው ልጅ በሥነ ምግባር ከፍታ ውስጥ እንዲኖር ያስችለዋል፡፡ ፆመኛ የሆነ ሰው አካሉ ሲደክም መንፈሱ እያደገ እየጎለበተ ይመጣል፡፡ ለፈጣሪ ታዛዥ እየሆነ በመጣ ቁጥር ሥነ ምግባሩም መልካም ይሆናል። ይህ ደግሞ የፆሙ ዋነኛ ዓላማ ሥነ ምግባርን ማስተካከል ነው፡፡ ፆመኛ የሆነ ሰው መጥፎ ንግግርን አይናገር፣ መጥፎ ተግባራትን አይፈፅም ሰው እንኳን ቢሰድበው ብሎም ሊገድለው ቢመጣ እንኳን ፆመኛ ስለሆነ ምንም አይናገርም፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ፆምን በሚፆምበት ወቅት የ11 ወሩን ስንቅ የሚይዝበት የለውጥ ስንቁን የሚያገኝበት ነውም ብለዋል፡፡
በአፅዋማት ወቅት የሚታዩ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ እሴቶች ከኃይማኖታዊ ይዘታቸው ባሻገር ለሀገር ግንባታ፣ ለኢኮኖሚ ብልጽግና እና ለህዝብ አንድነት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚናገሩት ደግሞ መጋቢ በለጠ ናቸው፡፡ እነዚህን እሴቶች ለሀገር በሚበጅ መልኩ ለማጠንከር ይቻል ዘንድ ራስን መግዛት፣ ለተቸገረ መራራት፣ ይቅር ባይነት እና ታማኝነት በኃይማኖት የታነጸ ዜጋ መገለጫዎች ናቸው። እነዚህ እሴቶች ከቤተ እምነቶች ቅጥር ግቢ አልፈው በስራ ቦታዎች፣ በገበያ ስፍራዎችና በፖለቲካዊ መድረኮች ላይ ተግባራዊ አድርጎ ማስቀጠል በዋናነት የሀገርን ሰላምና ብልጽግና በእጅጉ እንዲረጋገጥ የሚያግዝ ተግባር ነውም ብለዋል፡፡
“በአጿማት ወቅት ተግባራዊ የሚደረጉ እሴቶችን ለሀገር በሚበጅ መልኩ እንዴት ማጠንከር ይቻላል?” ተብለው ለተጠየቀው ጥያቄ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ ዘሪሁን ዶዳ (ዶ/ር) ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ሀገራችን ኢትዮጵያ በብዝሃ ማንነት ደምቃ ለዘመናት የሕዝቦችን አብሮነት በማስጠበቅ ረገድ ኃይማኖታዊ ብሎም ማህበራዊ እሴቶቿን አጠናክራ ማስቀጠል በመቻሏ ምክንያት ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ በተለያየ እምነት ውስጥ የሚገኙ አማኞችም ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎቻቸው በሚደግፈው አግባብ በሙሉ ስርዓቶችን እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ ወቅቱ የፆም መሆኑን ተከትሎም የሰው ልጆች እራሳቸውን የሚገዙበት የትኛው መልካም ተግባር ነው፡፡ የትኛውስ ነው ከፈጣሪ ጋር የሚያስታርቀኝ በሚል ወደ እራሱ መለስ ብሎ የሚጠይቅበት ወቅት ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡
እንደ ዘሪሁን (ዶ/ር) ገለፃ፤ በአፅዋማት ወቅት ተግባራዊ የሚደረጉ እሴቶችን ለሀገር በሚበጅ አግባብ ለመጠቀም ያስችል ዘንድ እንደሚከተለው ፋይዳውን ጠቅሰዋል፡፡ አንድ አማኝ ፆም በሚፆምበት ወቅት የሚከውናቸው በጎ ተግባራት እንደ መረዳዳት፣ አንዱ ለአንዱ ማዘን፣ ያለውን መካፈል፣ ፍቅር፣ ርህራሄ እና መሰል ነገሮችን ዘወትራዊ በማድረግ ሂደቱን ማፅናት ያስፈልጋል የሚል እምነት አላቸው፡፡ በተለይም በፆም ወቅት በብዛት የሚነበቡ መንፈሳዊ ትምህርቶችን የዕለት ተዕለት ተግባር በማድረግ ምንጊዜም መልካምነትን እና በጎነትን በመሻት ፈጣሪ በሚፈልገው አግባብ መመራት መቻል ያስፈልጋል የሚል ሐሳብ አላቸው፡፡
በጾም ወቅት የሚደረጉ የምጽዋት እና የቸርነት ተግባራት በሀገር ደረጃ የሚያስገኙት ውጤት እጅግ ትልቅ ነው። መረዳዳትና መደጋገፍን ከማስፋፋት አንጻርም የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት የሚደረጉ ጥረቶች በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይቀሩ፣ በተደራጀ መልኩ የደካሞችን ኑሮ የሚደግፉ የልማት ሥራዎች ላይ እንዲውሉ ማስቻያ መንገድ ጭምር ነው፡፡ ያለው ለሌለው መስጠት የሚችል ከሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ የኢኮኖሚ ልዩነትን የሚያጠብ ሥነ-ልቦና ይፈጥራል። ከዚህ ባሻገርም አብዛኛው የጾም ወቅት የይቅርታና የፍቅር ጊዜ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህን ለሀገር ሰላም እጅግ አበርክቶው የላቀ ያደርገዋል፡፡ የውይይት ባህልን በማዳበር ቅሬታዎችን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት እና ይቅር ባይነትን የማስቀደም ልምድ ለሀገራዊ መግባባት ትልቅ መሠረት አለውም ሲሉ ተናግረዋል።
በሄለን ጥላሁን