ከተማዋ በልማት ስራዎቿ ለነዋሪዎችና ለእንግዶች የተመቸች ዓለም አቀፍ መዲና ለመሆን መብቃቷ ተመላክቷል
አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና፣ የዲፕሎማቶች መቀመጫ እና የረጅም ታሪክ ባለቤት፣ የሚለው መጠሪያዋ ከከተማዋ የቀድሞ ገጽታ ጋር በእጅጉ ይጋጭ ነበር። ከዓመታት በፊት በመንገዶቿ ዳር የሚታዩ የቆሻሻ ክምሮች፣ አረንጓዴነት የጠማቸው ሰፈሮች እና የውበት መስፈርቶችን ያላሟሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከተማዋን በዓለም አቀፍ መድረክ ዝቅተኛ ግምት እንዲሰጣት አድርገዋት ቆይተዋል።
መዲናዋ ለብዙ ዓመታት የፅዳትና የአረንጓዴ ልማት ጉዳይ የቅንጦት ያህል ርቋት ከመቆየቱም በላይ በዓለም አቀፍ የከተሞች የኑሮ ጥራት መስፈርት (Livability Index) ግርጌ ላይ ተቀምጣ ቆይታለች፡፡ በአንድ ወቅት በአንዳንድ አካላት የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነቷን ትነጠቅ ዘንድ ሙግት ይቀርብ የነበረውም እነዚህን ጉዳዮች በመከራከሪያነት በማቅረብ ነበር፡፡
ከተማዋ የንግድና የዲፕሎማሲ ማዕከል ተደርጎ የሚወሰዱት እንደ ቸርችል ጎዳና፣ የቦሌ አውራ ጎዳናዎች፣ ሳርቤትና መሰል አካባቢዎች በአንድ ወቅት ከውበት ይልቅ በጭስና በአቧራ የተሸፈኑ ነበሩ። በታሪካዊው ማዘጋጃ ቤት ፊት ለፊት የሚዘረጉት መንገዶች በፅዳት እጦት የታወቁ፣ የእግረኛ መንገዶቻቸው ለንግድ እቃ መደርደሪያነት የተያዙና የከተማዋን ማንነት የማይወክሉ ነበሩ። ወደ ሜክሲኮና ፒያሳ አካባቢ ስናመራም፣ አረንጓዴ ፓርኮች ቀርቶ አንዲት ዛፍ ለማግኘት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ግድ ይል ነበር። እነዚህ አካባቢዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለከተሞች ውበትና ለአየር ንብረት ተስማሚነት የሚሰጠውን መስፈርት ማሟላት ቀርቶ፣ ለነዋሪዎቻቸው እንኳ የሚተነፍስ አየር የነፈጉ የነበሩ ስለመሆናቸው ለመናገር እማኝ ማፈላለግ አያስፈልግም፡፡
አዲስ አበባን አቋርጠው የሚያልፉት ወንዞች—በተለይም ቀበና፣ ቦሌ እና ባንቢስ አካባቢ የሚገኙት የከተማዋ የውበት ምንጭ መሆን ሲገባቸው፣ ለዓመታት የኢንዱስትሪና የቤቶች ቆሻሻ ማከማቻ ሆነው ቆይተዋል። ወንዞቹ ዳርቻቸው የቆሻሻ ተራራ የተከመረባቸው፣ ሽታቸው በአካባቢው ለማለፍ የሚፈታተንና ለበሽታ መፈልፈያነት የተጋለጡ ነበሩ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በወንዝ ዳርቻ ልማት የሚለኩ ከተሞች አዲስ አበባን ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጧትም እነዚህን የተፈጥሮ ጸጋዎቿን ወደ “ክፍት የፍሳሽ ማስወገጃነት” ቀይራቸው በመቆየቷ ነበር።
በመገናኛ፣ በካዛንቺስ እና በፒያሳ ያሉ የሕዝብ መተላለፊያዎች የቀድሞ ገጽታቸው የከተማነትን ትርጉም የሚጋፋ ነበር። ጠባብና የተሰባበሩ የእግረኛ መንገዶች፣ በዝናብ ወቅት በጭቃ የሚሞሉና በበጋው አቧራ የሚያስነሱ አውራ ጎዳናዎች የአዲስ አበባ መገለጫዎች ነበሩ። የከተማ ውበት የሚለካው በእግረኞች ምቾት ቢሆንም፣ በእነዚህ አካባቢዎች ግን ሰውና መኪና ተጋፍተው የሚውሉባቸው፣ የአካል ጉዳተኞችና ሕፃናት ታሳቢ ያልተደረጉባቸው፣ በአጠቃላይ ለዐይን የሚከብዱና ለከተማነት መስፈርት እጅግ ኋላ ቀር የነበሩ መልክዓ ምድሮች ነበሩ።
ወደ ሀገሪቱ መግቢያ በሆነው በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ዙሪያ እንኳ ሳይቀር፣ የሚታየው ገጽታ አረንጓዴነት የጎደለውና የተዝረከረከ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። በጎዳናዎች መካከል ያሉ ደሴቶች በደረቅ አፈር የተሞሉ እንጂ ሳርና አበቦች የደመቁባቸው አልነበሩም። ይህ የውበት ጉድለት ደግሞ ወደ ሀገር ውስጥ ለሚገቡ እንግዶች የመጀመሪያውና መጥፎው ስሜት ሆኖ ያገለግል ነበር። ከተማዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ “የአፍሪካ መዲና” የሚለውን ታላቅ ስም ብትሸከምም፣ በሰፈሮቿ ውስጥ የሚታየው የተፈጥሮና የሰው ሰራሽ ውበት መጓደል ግን ከስሟ በታች እንድትሰለፍ አድርጓት ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደሚገልጹት፣ አዲስ አበባ ለበርካታ ዓመታት በመሠረተ ልማት እጥረትና በቆሻሻ ክምችት የታወቀች፣ ለነዋሪዎቿም ሆነ ለጎብኚዎች የማትመች ከተማ ሆና ቆይታለች። በተለይም በወንዝ ዳርቻዎችና በሰፈሮች ውስጥ ይስተዋል የነበረው የፅዳት ጉድለት የመዲናዋን ዓለም አቀፋዊ ስም የሚመጥን አልነበረም። ይህንን ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር መንግሥት ቁርጠኛ አቋም በመያዝ፣ ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ ቆይቷል። ይህ ለውጥ ከተማዋን ከነበረችበት ዝቅተኛ ደረጃ አውጥቶ በዓለም አቀፍ መስፈርት ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለመ ነው፤ ግቡንም መትቷል።
በተለይም የኮሪደር ልማትና የአረንጓዴ ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ውበት ከመመለስ ባለፈ፣ የእግረኛ መንገዶችን በማስፋፋት፣ የብስክሌት መንገዶችን በመፍጠርና የወንዝ ዳርቻዎችን ወደ መዝናኛነት በመቀየር ነዋሪዎች ንፁህና አረንጓዴ አካባቢ እንዲኖራቸው የሚያስችሉ ናቸው። ይህ የልማት ጉዞ አዲስ አበባን “እንደ ስሟ አዲስ” የማድረግና ለትውልድ የሚተርፍ ዘላቂ የከተማ ውበት የመገንባት ሂደት መሆኑን ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች ይገልጸሉ።

የከተማ ልማት ምርታማነትን፣ ባህልን እና የሰው ልጆችን ደስታ ከፍ በማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት የከተማ ልማት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር እ.ኤ.አ በጥር 31 ቀን 2012 ‘የከተሞች እውነት ወይም ድል’ (Triumph of the City) በተሰኘው ጥናታዊ መፅሐፋቸው ላይ ገልጸውታል፡፡ በርካታ የዓለማችን ክፍል ቀን እንደነገሩ ውሎ አመሻሹን ሲያሸልብ ከተሞች ግን በተራራ ላይ እንደተለኮሰ ችቦ ብርሃንን እየፈነጠቁ በምድርቱ ላይ ያረበበውን ጨለማ እንደ አደይ አበባ በፈካ ውበታቸው እንዴት እንደሚገፍፉት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ባማረ አገላለፅ፣ “ከተሞች የዓለማችን ሕይወት መቀጠል ምልክት፣ የልብ ትርታችን ምት ናቸው” በማለት በመፅሐፋቸው ከሽነውታል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን ቅኝት ያደረገባቸው የተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የከተማ ልማት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር “ከተሞች የዓለማችን ሕይወት መቀጠል ምልክት፣ የልብ ትርታችን ምት ናቸው” በማለት ካስቀመጡት ጭብጥ ጋር የሚደጋገፍ ይመስላሉ፡፡ ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት ወርደን ወደ መስቀል አደባባይ ስናቀና፣ መንገዱን በግራና ቀኝ አጅበው የሚገኙት የቆዩ ሕንፃዎች አዲስ ልብስ የለበሱ ይመስላሉ። በአንድ ወቅት በአቧራና በጭስ ጠቁረው፣ የእግረኛ መንገዶቻቸው ተሰባብረው የነበሩት እነዚህ ጎዳናዎች፣ ዛሬ ሰፋፊና ጽዱ በሆኑ የእግረኛ መንገዶች ተተክተዋል።
በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ለረጅም ዓመታት በንግድ ሥራ የሚተዳደሩት አቶ ካሳሁን ያለው እንደሚሉት ከሆነ፣ ለውጡ ለዓይን ካለው ውበት ባለፈ ለሥራ ያላቸውን ተነሳሽነት ጨምሮላቸዋል። “ቀድሞ በዚህ መንገድ ላይ በእግር መጓዝ ራሱ አድካሚ ነበር፤ ዛሬ ግን መንገዱ ራሱ ጋባዥ ሆኗል። የከተማችን ክብር የተመለሰልን ያህል ይሰማኛል” ይላሉ።
ወደ ኦሎምፒያና ወሎ ሰፈር ስንዘልቅ ደግሞ የኮሪደር ልማቱ ያመጣው ትልቁ ድል የቦታ አጠቃቀም ሥርዓት መያዙን ነው። ቀድሞ መኪናና እግረኞች ተቀላቅለው በሚጨናነቁባቸው በእነዚህ አካባቢዎች፣ ዛሬ ለብስክሌት ተጓዦችና ለምሽት ተላላፊዎች የተመቹ ዘመናዊ መብራቶችና የአረንጓዴ ስፍራዎች ተፈጥረዋል። የወሎ ሰፈር ነዋሪ የሆነችው ወጣት ሰላም መኩሪያ በበኩሏ “ከዚህ በፊት ምሽት ላይ በእነዚህ መንገዶች ማለፍ ደህንነት አይሰማም ነበር። አሁን ግን መብራቶቹና መንገዱ ያለው ግልጽነት ከተማዋን የሰላም መናኸሪያ አድርጓታል። እንደ ማንኛውም ዘመናዊ ከተማ በነፃነት የምንዘዋወርበት ድባብ ተፈጥሯል” ስትል ትዝብቷን አካፍላኛለች።
ወደ ቦሌ ኤርፖርት በሚያደርሰው ሰፊ ጎዳና ላይ ስንደርስ፣ የአዲስ አበባ ‘የመግቢያ በር’ መሆኗ በተግባር መረጋገጡን እናስተውላለን። በደረቅ አፈርና በባዶ ቦታዎች ተሸፍነው የነበሩት የመንገድ ዳርቻዎች እና አካፋዮች ዛሬ በተለያዩ አበቦችና ለምለም ሳሮች አጊጠዋል። ይህ ለውጥ ከከተማ ውበት ባለፈ የመዲናዋን ዲፕሎማሲያዊ ገጽታ ከፍ የሚያደርግ ነው። ዝግጅት ክፍላችንም በቦታው ተገኝቶ ባደረገው ቅኝት የተረዳው ትልቁ እውነት፣ ይህ የኮሪደር ልማት ለነዋሪው ሕዝብ ክብርን የሰጠ፣ የከተማዋን መንፈስ ያደሰና አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ መድረክ የነበራትን ዝቅተኛ የውበት ደረጃ ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገረ ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ነው።
አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዝቅተኛ የውበት ደረጃ እንድትመደብ ካደረጓት ምክንያቶች አንዱ የከተማ ፕላኗ ሰውን ማዕከል ያላደረገ መሆኑ ነበር። ቀደም ባሉት ዓመታት የመንገድ ልማቶቻችን ትኩረት ያደርጉ የነበረው መኪናን ለማሳለፍ ብቻ በመሆኑ፣ እግረኛው በጭቃና በአቧራ መካከል እንዲጋፋ ይገደድ ነበር። የኮሪደር ልማቱ ግን ይህንን የተዛባ አመለካከት በመቀየር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሁሉንም የሚያካትት ከተማ የሚባለውን መስፈርት ተግባራዊ አድርጓል። ከአራት ኪሎ እስከ ቦሌ የሚታዩት ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶችና ማረፊያ ወንበሮች፣ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ያላትን ክብርና የውበት ደረጃ ከፍ ማድረጋቸውን የሚያሳዩ የለውጥ ማሳያዎች ናቸው።
በፕሮፌሰር ኤድዋርድ ግሌዘር እ.ኤ.አ ጥናታዊ መፅሐፍ ማብራሪያ መሠረት፣ የአንድ ዘመናዊ መዲና ውበት የሚለካው በቀን ብቻ ሳይሆን በምሽት በሚኖራት ገጽታም ጭምር ነው። አዲስ አበባ በምሽት ጨለማ የሚነግስባትና ለደህንነት የማትመች ከተማ ተብላ የምትፈረጅበት ጊዜ አብቅቷል። በኮሪደር ልማቱ የተገጠሙት ዘመናዊና ኃይል ቆጣቢ የጎዳና ላይ መብራቶች እንዲሁም በሕንፃዎች ላይ የተገጠሙ የጌጥ መብራቶች፣ ከተማዋን በምሽትም እንድትፈካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ‘ስሉጥ ከተማ’ (Smart and Safe City) ከሚባሉት መመዘኛዎች ጋር እንድትቀራረብ አድርጓታል።
በአረንጓዴ ልማት ረገድ የኮሪደር ልማቱ ያበረከተው ትልቁ አስተዋጽኦ የከተማ ደን ልማትን ወደ ጎዳናዎች ማምጣቱ ነው። ቀደም ሲል ለከተማ ውበት ተብለው የሚተከሉ ዛፎችና አበቦች ዘላቂነት የሌላቸውና በዘፈቀደ የሚተከሉ ነበሩ። አሁን ግን የአፈርን ለምነትና የአካባቢውን የአየር ንብረት ከግምት ውስጥ ያስገቡ የዕፅዋት ዝርያዎች በስፋት መተከላቸው፣ ከተማዋን የካርቦን ልቀትን የምትከላከል አድርጓታል። ይህም አዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘላቂ ከተማ ለመባል የምታደርገውን ጥረት የሚያፋጥንና የአየር ጥራት መስፈርቶችን እንድታሟላ የሚረዳ ተግባር ሆኖ ተመዝግቧል።
አንድ ከተማ በዓለም አቀፍ መስፈርት ከፍ ያለ ደረጃ ሲሰጠው፣ የቱሪስት መስህብነቱና የኢንቨስትመንት ፍሰቱም አብሮ ይጨምራል። አዲስ አበባ የዲፕሎማቲክ መናኸሪያ እንደመሆኗ፣ የኮሪደር ልማቱ የፈጠረው ጽዱና ሳቢ ገጽታ ለሀገር ገጽታ ግንባታ ትልቅ ፋይዳ አለው። የቦሌ ዓለም አቀፍ አየር መንገድን ተሻግሮ ወደ ከተማዋ የሚገባ እንግዳ፣ ዛሬ የሚቀበለው የተቀናጀ የሕንፃዎች ውበት፣ የተስተካከሉ የአረንጓዴ ስፍራዎችና ጽዱ ጎዳናዎች ናቸው። ይህ ለውጥ ከተማዋን ከድህነትና ከዝቅተኛ ደረጃ ተምሳሌትነት አውጥቶ፣ ወደ ዘመናዊነትና ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ ለዓለም የሚያበስር ተግባራዊ ምስክርነት ነው።
አንዳንድ ከተሞች ከድንበራቸው ባለፈ የዓለም ዕጣ ፈንታ የሚወሰንባቸው፣ የታሪክ አቅጣጫ የሚቀየርባቸውና የኃያላን መሪዎች መገናኛ የመሆናቸው ምስጢር በድንገት የሚከሰት አይደለም። አንድን ከተማ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ለመሪዎች ተመራጭ የሚያደርጓት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከተማዋ ያላት አንጻራዊ የሰላም ሁኔታና የደህንነት አስተማማኝነት እንደ ዋነኛ መስፈርት ይወሰዳል። መሪዎች በነጻነት የሚመክሩባት፣ የዲፕሎማሲያዊ ጥበቃና ከለላ የተረጋገጠባት ከተማ ሁልጊዜም የሁለንተናዊ ትብብር መፍለቂያ ትሆናለች።
ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ በርካታ የሀገር እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች አዲስ አበባን ጎብኝተዋል፤ እነዚህም የላይቤሪያ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ጆሴፍ ንዩማ ቦአካይ፣ የቡሩንዲ ፕሬዝዳንት ኢቫሪስቴ ንድያይሺሚዬ፣ የፖርቹጋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፓውሎ ራንገል እና የአፍሪኤግዚም ባንክ ፕሬዝደንት ዶክተር ጆርጅ ኢሎምቢ ናቸው፡፡ መሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ ቆይታቸው የከተማዋን የልማት ፈርጦች ጎብኝተዋል። መሪዎቹ በጉብኝታቸው ወቅት አዲስ አበባ በየቀኑ መልኳን እየቀየረች ያለች ድንቅ ከተማ ሆናለች በማለት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ከተሞችን በዘመናዊ መልክ መልሶ ማልማት የኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ወሳኝ ሚና እንዳለው የሚገልፁት ደግሞ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት በረከት አድማሱ ናቸው፡፡ መምህሩ ከኤኤምኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ ከተማን ማዘመን የኢኮኖሚ እድገት ቀጥተኛ መገለጫ ነው። ከተሞች ሲዘምኑ የንግድ እንቅስቃሴዎች ይነቃቃሉ፣ የኢንቨስትመንት ፍሰትም ይጨምራል። በፊት ለመተላለፊያ እንኳን የማይበቁ መንገዶች በልማቱ ምክንያት በመስፋፋታቸው፣ ሰፊ የመንገድ አማራጮች መፍጠር ያስችላሉ ብለዋል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ