AMN መጋቢት 07/2018 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ኢትዮጵያ የብዝሃ-ሃይማኖት አገር ናት በማለት ባስተላለፉት መልእክት “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግሥት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶችና አመራሮች ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዛሬዋን ኢትዮጵያ በመገንባት ረገድ ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ወሳኝ ሚና አበርክታለች። ቤተክርስቲያኗ በሀገረ መንግሥት ግንባታ፤ ጥንታዊ ቅርሶችን፣ ታሪኮችንና ትውፊቶችን ጠብቆ ለትውልድ በማሸጋገር፤ ትውልድን በማነጽ፤ ግብረ-ገብነትንና ሰብአዊ ርኅራኄን በማስተማር፤ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን በማጠናከር እንዲሁም በልማት ተሳትፎ የጎላ ድርሻ ስትወጣ ቆይታለች።
በታሪክ ብቻ ሳይሆን ባለፉት የለውጥ ዓመታትም ቤተክርስቲያኗ በከተማችን ሁለንተናዊ የሰላም ግንባታ፣ የልማት እና የብልፅግና ጉዞ ላይ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ አንስተን የተወያየን ሲሆን፣ ለሕዝቦች ትስስር መጎልበት፣ ለሰላም ፣ ለኢትዮዽያ ብልፅግና እና ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ ለመቆም መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል፡፡

የዉይይት መድረኩ፣ የተነሱ አንዳንድ ያጋጠሙ ክፍተቶችን በትብብር ለማረም የሚያስችል ምቹ መደላድል የፈጠረ ውጤታማ መድረክ ነበር። ይህ መድረክ በየክፍለ ከተማው ሲካሄዱ የቆዩ ውይይቶች ማጠቃለያ ሲሆን፣ የመንግሥትንና የሃይማኖት ተቋማትን ሚና እና ድርሻ በግልጽ ለይቶ ያስቀመጠ ነው።
ክቡራን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አባቶችና አመራሮች፤ ላደረጋችሁት ከፍተኛ ተሳትፎና ለሰጣችሁን ገንቢ ሐሳብ በራሴና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ። መልካም የአብይ ጾም! ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡