AMN መጋቢት 7/2018
የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት የአካባቢ ጥበቃን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር በኩል ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በአርዓያነት የሚወስዱት መሆኑን የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን አባላት ሀገራት ተወካዮች ገለፁ።
የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን አባል ሀገራት ተወካዮች የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማትን ጎብኝተዋል። በጉብኝቱ ወቅት የመዲናዋን የወንዝ ዳርቻዎችን በማልማት ከቆሻሻ መጠራቀሚያነት ወደ ሕዝብ መዝናኛነትና የከተማ ውበት አካል እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን አድንቀዋል።
በተለይም የወንዝ ዳርቻዎችን አረንጓዴ በማልበስ የአካባቢ ጥበቃን ከቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር በኩል ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት እንደሚሆን ገልጸዋል።
የዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ፌሊክስ ሞሲ ንጋምላጎሲ፥ የአፍሪካ ከተሞች የታቀዱ፣ ሳቢ እና የቱሪስት መዳረሻዎች እንዲሆኑ በማድረግ በኩል አዲስ አበባ በአርዓያነት የምትጥቀስ ናት ብለዋል።
በተለይም አሁን ላይ በአዲስ አበባ እየታዩ ያሉ ለውጦች ከተማዋን ለመዝናኛና ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተመራጭ እያደረጓት መሆኑን ተናግረዋል። ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ካሉ የልማትና የከተማ ውበት ስራዎች ልምድ እንዲቀስሙና ትምህርት እንዲወስዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚምባብዌ የመጣችው ቺቶ ፊሪ በበኩሏ የአዲስ አበባ የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮች በስፋት ተገንብተው መመልከቷን በአድናቆት ጠቅሳለች። ይህም ለከተማዋ ድምቀት ከመሆኑ ባለፈ ለነዋሪዎችና ለጎብኚዎች ምቹ የመንቀሳቀሻ ከባቢን የሚፈጥር ነው ብላለች።

በአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻና የኮሪደር ልማት ለእግረኛ መንገድ የተሰጠው ትኩረት ለጤና እጅግ ተስማሚ የሆነውን የእግር ጉዞ ባህል ለማነቃቃት ትልቅ ዕድል መፍጠሩንም ነው የተናገረችው።
ከሞዛቢክ የመጡት ማኑኤል ቻጉሎ ከ15 ዓመታት በፊት ኢትዮጵያን ጎብኝተው እንደነበር በማስታወስ፤ አሁን ድጋሚ ሲመጡ አዲስ አበባ አስድናቂ ለውጥና ዕድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ልማት ልምድ የሚቀሰምበት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቷን ጨምረው መጥቀሳቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡