አዲስ አበባ የታሪክ ከተማ ብቻ ሳትሆን የተስፋ እና የብልጽግና ተምሳሌት መሆኗን ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች ገለጹ

You are currently viewing አዲስ አበባ የታሪክ ከተማ ብቻ ሳትሆን የተስፋ እና የብልጽግና ተምሳሌት መሆኗን ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች ገለጹ

AMN- መጋቢት 7/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግብዣ በተዘጋጀ የጉብኝት መርሐ ግብር ላይ የተሳተፉ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ጋዜጠኞች፤ አዲስ አበባ የታሪክ ከተማ ብቻ ሳትሆን የተስፋ እና የብልጽግና ተምሳሌት መሆኗን ገለጹ።

ጋዜጠኞቹ በቆይታቸው የኮሪደር ልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎችን ጨምሮ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነባውን አዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽን ማዕከል፣ የእንጦጦ እና የአራዳ ፓርኮችን እንዲሁም የአድዋ ድል መታሰቢያን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት ጋዜጠኞቹ እንደተናገሩት በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች አዲስ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እየፈጠሩ ይገኛሉ።

በጉብኝቱ ላይ የተሳተፈችው ግብፃዊቷ ጋዜጠኛ ጃኪ ሀቢባ በሰጠችው አስተያየት፣ በከተማዋ ባለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ውስጥ የተመዘገበው የመሠረተ ልማት ለውጥ እጅግ አስገራሚ መሆኑን ገልጻለች።

ጋዜጠኛዋ አክላም በከተማዋ የተገነቡት ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ የመንገድ ዳር መብራቶች፣ የተሽከርካሪ መንገዶች እና ዘመናዊ የመኖሪያ መንደሮች አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ሳቢ እያደረጓት መሆኑን አብራርታለች።

ሌላው ናይጀሪያዊው ጋዜጠኛ አማኑኤል አኪንዱብዋ፤ አዲስ አበባ የአፍሪካ ኩራት መሆኗን በተግባር ማረጋገጡን ገልጾ፣ የልማት ሥራዎቹ ዘርፈ-ብዙና ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተቱ መሆናቸውን አድንቋል።

በተለይም የልማት ሥራዎቹ ሴቶችን ማዕከል ማድረጋቸው ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ አርአያ ሊሆን የሚችል መሆኑን ጠቁሟል።

ከማዳጋስካር የመጣችው ጋዜጠኛ ላላኢና ሪንድሪአርማናና በበኩሏ፣ ከከተማዋ ገጽታ መለወጥ ባለፈ ነዋሪዎች ያሳዩአቸው እንግዳ ተቀባይነትና ወዳጅነት ወደ ቤታቸው እንደገቡ ያህል እንዲሰማቸው ማድረጉን ገልጻለች።

አዲስ አበባ በምሽት ያላት ውበት፣ ንጽህና እና አስተማማኝ ደኅንነት ከተማዋን መጎብኘት ለሚፈልግ ማንኛውም ሰው ተመራጭ እንደሚያደርጋትም በጉብኝቱ ወቅት ተመላክቷል።

ጋዜጠኞቹ በስተመጨረሻም፣ የተመለከቱትን እውነተኛ የአፍሪካ ስኬት ታሪክ በየሀገራቸው ለሚገኙ የሚዲያ ተቋማትና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማስተዋወቅ እውነታውን እንደሚያበስሩ ቃል ገብተዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review