AMN – መጋቢት 9/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የልማት አጋርነታቸውን የሚያጠናክር እና የኢትዮጵያን የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚደግፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ለማገዝ በተደረገው በዚህ ትልቅ እርምጃ የኢፌዴሪ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና የጣሊያን ሪፐብሊክ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ሚኒስትር ጃንካርሎ ጆርጌቲ የሁለትዮሽ የዕዳ ሽግሽግ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ ስር ይፋዊ አበዳሪዎች ኮሚቴ (OCC) በሚመራው ማዕቀፍ መሠረት የተከናወነ ነው።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ለጣሊያን መንግስት ገንቢ ተሳትፎ እና አመራር ምስጋናቸውን አቅርበዋል። ይህም እ.ኤ.አ. በሐምሌ 2025 የተደረሰውን የመግባቢያ ሰነድ እንዲሁም አሁን የተፈረመውን የሁለትዮሽ ስምምነት በስኬት ለማጠቃለል ወሳኝ ሚና እንደነበረው ገልጸዋል።
የጣሊያን ሚኒስትር በበኩላቸው፣ ስምምነቱ ከኢትዮጵያ የማክሮ-ኢኮኖሚ ማሻሻያ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር ሀገር በሆነችበት የጣሊያን “ማቲ ፕላን ለአፍሪካ” ስኬት የራሱን አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት መግለጻቸውን ሚኒስቴሩ ለኤ ኤም ኤን የላከው መረጃ ያመለክታል።