• በአዲስ አበባ ከተማ የከተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራ እንደ ኢድ አልፈጥር ላሉ በዓላት ድርብ ድምቀት እንደሚሰጥ ተመላክቷል
አዲስ አበባ እንደ መስከረም ፀሐይ ደመናውን ጥሳ፣ እንደ አደይ አበባ ውበትን ተላብሳ እንደ ንስርም በፍፁም ታድሳ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበች እንደሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ በመመስከር ላይ ናቸው፡፡ ለዚህም በቅርቡ የኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት “የአፍሪካ ከተሞች በ2035” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ነሐሴ 23 ቀን 2024 ይፋ ያደረገውን መረጃ በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በዚሁ መረጃ መሰረት አዲስ አበባን ጨምሮ ስድስት ከተሞች በ2035 ወደ ሜጋ ከተማነት ያድጋሉ። ይህ ግምት የተሰጣቸው አዲስ አበባ፣ ሪዮ ዲጄኔሮ፣ ዳሬሰላም እና ኪጋሊ ናቸው።
“በርግጥም ስለአዲስ አበባ አስገራሚ ለውጥ ለመናገር ምስክር አያሻም፤ ምክንያቱም ከተማዋ እንደስሟ አበባ እየሆነች ስለመምጣቷ የተመለከታት ሁሉ ምስክር ነው፡፡” ይላሉ የመዲናዋ ነዋሪ አቶ አህመድ ከማል፡፡ በመዲናዋ ከ35 ዓመታት በላይ እንደኖሩ የነገሩን አቶ አህመድ እንደሚሉት ከተማዋ ቀደም ባሉት ዘመናት ነግዶ ለማትረፊያ እንጂ ያን ያህል ለመኖሪያ ምቹ እንዳልነበረች ተናግረዋል፡፡
የዚህን ምክንያት ሲያብራሩም፣ ንፅህናቸውን ያልጠበቁ መንገዶችና መንደሮች በብዛት ከመኖራቸውም በላይ በአንዳንድ አካባቢዎች ክረምት በመጣ ቁጥር አሊያም ሙቀቱ በሚያይልባቸው ወቅቶች ወረርሽኞች ጭምር ይከሰቱ እንደነበር አስታውሰው አሁን በከተማዋ እየተከናወነ ባለው ልማት እነዚህ ችግሮች እየተፈቱ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
አሁን ከተማዋ ለንግድ ብቻ ሳይሆን ለመኖሪያም የምትመረጥ፣ ጎዳናዎቿ የሚያምሩ ውብ ከተማ ሆናለች፡፡ በዚህ ላይ እንደ ኢድ አልፈጥር የመሳሰሉ በዓላትን ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ሲያከብር ከህብረ ቀለማቱ ውበት ጋር የተዳመረ ገፅታዋ ጎልቶ ሲወጣ እጅጉን ታምራለች ይላሉ አቶ አህመድ፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ባሻ ወልዴ ተብሎ የሚጠራ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፎዚያ አህመድ በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ውበት ነግቶ በጠባ ቁጥር አዲስ እየሆነ ነው ይላሉ፡፡ መንገዶች ከመዋባቸው የተነሳ አንዳንድ የማውቃቸው ስፍራዎች ጭምር ግር እያሉኝ መጥተዋል የሚሉት ወይዘሮ ፎዚያ፣ ይህን መሰል ለውጥ ከእኛ ባሻገር ለልጆቻችን እና ለልጅ ልጆቻችን ትልቅ ሀብት እንደማስቀመጥ ነው፡፡ በተለይም እንደ ኢድ አልፈጥ ያሉ ኃይማኖታዊም የሆኑ ሌሎች በዓላትን በአደባባይ ወጥተን ስናከብር የከተማዋ አሁናዊ ገፅታ ደስታችንን አይረሴ ያደርጉታል ብለዋል፡፡
የፎክሎር ባለሙያው አቶ ግዛው ማሞ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት በዛ ያሉ ቢሆኑም በተለይ እንደ ኢድ አልፈጥር ኃይማኖታዊ በዓላት በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች በድምቀት የሚከበሩና የማህበረሰቡን እሴት በጉልህ የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡
በእነዚህ በዓላት የሚታደሙ ኢትዮጵያውያን በተለይ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች እና አደባባዮች ሲታዩ ህብረ ብሔራዊነት ነፍስ ዘርቶ የሚደምቅበት፣ የማህበረሰቡ የተለያዩ ውብ ኃይማኖታዊ ስርዓቶች እና ባህላዊ አልባሳትና ጭፈራዎች በመዲናዋ አደባባይ የኢትዮጵያውያንን መልክና ልክ አጉልተው ሲያሳዩ በርካታ ጎብኝዎችን ቀልብ ይስባሉ፡፡

አዲስ አበባ እንደ አዲስ ውበቷ እየፈካ፣ ጎዳናዎቿ እንደ ፅጌሬዳ አበባ የሚያሳሱ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ ታዲያ በእነዚህ ውብ ጎዳናዎችና አደባባዮች ላይ እንደ ኢድ አልፈጥር የመሳሰሉ ኃይማኖታዊ በዓላት ሲከበሩ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን ለበዓላቱ ደግሞ ድርብ ድምቀትን ይሰጣሉ፡፡
ኃይማኖታዊም ሆነ የህዝብ በዓላት ህዝቡ በክት ልብሱ ደምቆ፣ መልካም መንፈስን ታጥቆ እና ከቤቱ ወጥቶ የሚያከብራቸው በዓላት በመሆናቸው በህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ናቸው፡፡ ታዲያ የበዓላቱና የአደባባዮቹ ድምቀት አብሮ ሲደመር ለከተማዋ ትልቅ ፍካትን ይፈጥራሉ፡፡ የማህበረሰቡም መልካም እሴቶች እንዲጎለብቱም ዕድል ይሆናሉ ይላሉ የፎክሎር ባለሙያው አቶ ግዛው ማሞ፡፡
የኢትዮጵያውያን ውብ ባህላዊ እሴቶች እንዲህ ደምቀው በአደባባይ ሲታዩ፣ ለሌላው ዓለም የህዝቡን መልካም ገፅታ እንዲሁም የሀገርን ሁለንተናዊ ከፍታ ያሳያሉ፡፡ እየለማ ያለው ግዑዝ የሆነው ቦታ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡም ነባር እሴት በመሆኑ በማህበረሰባዊ፣ በኢኮኖሚያዊም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ አበባ አስደናቂ ለውጥ እያስመዘገበች ያለች ሲሆን፣ ለዚህ ለውጥ በዋቢነት የሚነሳው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ነው። ይህም የከተማዋን አካላዊ ገጽታ በመቅረጽ ብቻ ሳይሆን ኃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላት በሚያምሩ ጎዳናዎች እንዲከበሩና ከፍ ብለውም እንዲታዩ በር የከፈተ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
የኮሪደሩ ልማቱ፤ የአዲስ አበባን መሠረተ ልማት ለማዘመን እና የበለፀገ የባህል ቅርሶቿን በመጠበቅ ላይ ያለመ የከተማ ፕላን ፕሮጀክት ስለመሆኑ የገለፁት አቶ ግዛው ይህም ልማት አዳዲስ መንገዶችን፣ መናፈሻዎችን እና የህዝብ ቦታዎችን መገንባትን ያጠቃልላል። ከመሰረተ ልማት ባሻገርም ከተማዋ ኃይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ በዓላትን በከፍታቸው ልክ የማስተናገድ አቅም እንዲኖራት አድርጓልም ብለዋል፡፡
ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ የበለጠ እርካታን ከመፍጠሩ በላይ ለባህልና ወጉ ያለው ፍቅርና አክብሮት እንዲጎለብት ያደርጋል፡፡ ለአብነትም በኢድ አልፈጥር በዓል የመዲናዋ የእስልማና እምነት ተከታዮች በተለያዩ አልባሳት እና ኃይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ ተውበው እንደሚደምቁ አስታውሰው፣ አሁን ደግሞ የመዲናዋ መንገዶች በኮሪደር ልማት እጅግ በመዋባቸው በዓሉ ከመቼውም ጊዜ ለየት ባለ መልኩ ማራኪ ገፅታ እንደሚኖረውም ተናግረዋል፡፡
ኃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት ሰዎች ልባቸውንም፣ ልብሳቸውንም አፅድተው በህብረት የሚያከብሯቸው በመሆኑ ንፁህ ስፍራዎችም ያስፈልጓቸዋል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ያስገኘው አንዱ በረከትም ለእነዚህ በዓላት ምቹ ማክበሪያ ቦታዎችን ነው፡፡ በመሆኑም የማህበረሰቡን ስጋና ነፍስ ለማስደሰት ትልቅ አቅምን ፈጥሯል። ይህም ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ለበዓላቱም አይረሴ ድምቀት ነውም ብለዋል፡
አክለውም ማህበረሰቡ በእነዚህ ስፍራዎች የአደባባይ በዓላትን ያለምንም መጨናነቅ በፍፁም ደስታና ውበት ሲያከብር ሀገራዊ ኩራት እንዲሰማው ይሆናል፡፡ የተሰራው ልማት ለእርሱ እንደሆነም በሚገባ እንዲረዳው፣ ልማቱንም እሴቶንም እንዲጠብቅና እንዲያከብር ያነሳሱታል፡፡
ወጣት እንድሪስ ጀማል በበኩሉ በኮሪደር ልማቱ ውብ ገፅታን የተላበሱት አዲሶቹ ቦታዎች ዝም ብለው የተገነቡ ሳይሆኑ ባህላችንን የምናከብርባቸው፣ ሰዎች ተሰብስበው የሚዝናኑባቸው መሆናቸውን ስለመታዘቡም አጫውቶናል፡፡ “የአደባባይ በዓላት ከመንፈሳዊ አስተምህሮው ባሻገር የባህላችን ማሳያዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም የኮሪደር ልማቱ በዓላቱን ከመቸውም ጊዜ በላቀ መልኩ እንድናከብራቸው የሚያስችለን ነው” ብሏል፡፡

የፎክሎር ባለሙያው አቶ ግዛው ማሞ እንደሚሉት፣ በከተማዋ ተከናወነው ኮሪደር ልማት ባህልን የጠበቀ የዘመናዊ ጉዞን እየተከተለች መሆኑንም የሚያመላክት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከእራሱ ጋር የታረቀ፣ እሴቱንና ወጉን የጠበቀ ማህበረሰብን ለመገንባት ትልቅ ጉልበት አለው፡፡
ከተማዋ ለሕዝባዊ በዓላት አዲስና ደማቅ ቦታዎችን በመፍጠር መሰረተ ልማቷን ከማዘመን ባለፈ ባህላዊ ማንነቷን እያጠናከረች ትገኛለች። የከተማዋ መሠረተ ልማት ማሻሻያዎች ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገቷን ከመደገፍ ባለፈ ለባህላዊ ቅርሶቿ አዲስ አድናቆት እንዲኖራት አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በነዚህ በታደሱ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ በዓላት እና ህዝባዊ ዝግጅቶች ሲካሄዱ፣ አዲስ አበባ የከተማ ልማት ከባህላዊ ጥበቃ ጋር እንዴት ሊጣጣም እንደሚችል ከሀገር ባለፈ እንደ አህጉርም ተምሳሌት ያደርጋታል ብለዋል።
በርካታ ሀገራት ጎዳናዎችን፣ አደባባዮችን እና መናፈሻዎችን ወደ ደማቅ የበዓል ማክበሪያ ማዕከልነት በመቀየር ባህሎቻቸውን እያሳደጉ እና እያበለጸጉ ነው፤ ይላል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) The Impact of Heritage Conservation on Cultural Development በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ መስከረም 26 2025 ይፋ ያደረገው መረጃ፡፡
ለአብነትም ጃፓን፣ ስፔን እና ዩናይትድ ስቴትስ – ህዝባዊ በዓላቶቻቸው ከፍ ብለው እና ደምቀው እንዲታዩ ጎዳናዎቻቸውን እና አደባባዮቻቸውን በማስዋብ ዓለም አቀፍ ትኩረትን መሳብ ችለዋል፡፡
ጃፓን፣ ቶኪዮን በመሳሰሉ ከተሞቿ በየዓመቱ የሚከበሩት የአደባባይ በአላቶቿ በሰፋፊ አደባባዮች፣ መንገዶችና ፓርኮች ላይ የበዓሉ ታዳሚዎች በአበቦች፣ በዛፎች እና በውብ ፏፏቶዎች ደስ ብሏቸው እንዲያሳልፉ ታደርጋለች። ይህም በመላው ዓለም በዓላቱ ትኩረት እንዲስቡ ምክንያት እንደሆነም በመረጃው ተመላክቷል፡፡
በዓለም ዙሪያ የባህል እና የፈጠራ ኢንዱስትሪዎች በየዓመቱ ከ2 ነጥብ 25 ትሪሊዮን ዶላር በላይ ያመነጫሉ፤ ይህም ወደ 30 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድልም ይፈጥራል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ የባህል ቱሪዝም ከዓለም ጉዞዎች ውስጥ 40 በመቶውን ይሸፍናል፡፡ በመሆኑም የኮሪደር ልማቱ የፈጠረው ውብና ምቹ ገፅታ በየዓመቱ ለሚከናወኑ ኃይማኖታዊ እና ህዝባዊ በአላት አይረሴ ትዝታን እና ተናፋቂ ድባብን ከመፍጠራቸው ባሻገር ከተማዋ በባህል ቱሪዝም ዘርፍም የበለጠ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ዕድልም የሚፈጥር ነው፡፡
በመለሰ ተሰጋ