የአብሮነት ድምፅ

You are currently viewing የአብሮነት ድምፅ

መንዙማ ከሃይማኖታዊ ማስተማሪያነት ባለፈ፣ ጥልቅ የሆነ ማህበራዊ ፋይዳ ያለው ጥበብ ነው። መንዙማ “ነዘመ” (ደረደረ/ሰደረ) የሚል ትርጉም ካለው የአረብኛ ቃል የተወረሰ ሲሆን፣ ትርጉሙም በሥነ ስርዓት የተሰደረ ግጥም ወይም ውዳሴ ማለት ነው። በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ መንዙማ የእስልምናን አስተምህሮ፣ የነቢዩ መሐመድን ታሪክና የውልደት በዓል (መውሊድ)፣ እንዲሁም የደጋግ ሰዎችን ገድል ለሕዝቡ በቀላልና ማራኪ በሆነ መንገድ ለማድረስ የሚጠቅም ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ ለዘመናት አገልግሏል።

ይህ ጥበብ በታሪክ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ሙስሊም ሊቃውንት ውስብስብ የሆኑ ትምህርቶችን ለሕዝብ ቀላል በሆነ መንገድ ለማስተማር የተጠቀሙበት ስልትም ነው። ሊቃውንቱ ጥንታዊ የአረብኛ ቃላትን ከአገሬው ቋንቋዎች ጋር በማዋሃድ ትውልድ ተሻጋሪ እውቀትን አስተላልፈውበታል።

የተለያዩ መሳሪዎችን በመጠቀም የሚቀርቡት እነዚህ መንፈሳዊ ውዳሴዎች፣ አድማጭን ከመሳብ ባለፈ የውስጥ ሰላምንና መንፈሳዊ መነሳሳትን የመፍጠር አቅም አላቸው። መንዙማ የግጥም ይዘቱ የሰው ልጅን ሥነ-ምግባር የሚያርም፣ ዓለማዊ ሕይወት አላፊ መሆኑን የሚያስታውስና ግብረ-ገብነትን የሚሰብክ፣ አብሮነትን የሚያስተምር፣ ፍቅርና አንድነትን የሚያጎላ፣ የመከባበርና መመካከር ፋይዳን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ እንደ ትልቅ የማህበረሰብና ሀገር ግንባታ መሳሪያ ይታያል።

መንዙማ ከማህበራዊ ፋይዳው አንጻር የአንድነትና የመረዳዳት፣ የአብሮነትና የመከባበር ምልክት ነው። በመውሊድ በዓላትና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ ስርዓቶች ላይ ሰዎች በጋራ በመሰብሰብ፣ አንዱ አውራጅ ሌላው ተቀባይ በመሆን የሚያሳዩት ስርዓት በማህበረሰቡ መካከል ያለውን ትስስር ያጠናክራል። ይህም መንዙማ ከግል መንፈሳዊ እርካታ ባለፈ፣ የጋራ ማንነትንና ባህላዊ እሴትን ጠብቆ ለማቆየት የሚጫወተው ሚና የላቀ መሆኑን ያሳያል።

የመንዙማና ነሽዳ ባለሙያው አሚር መሐመድ የመንዙማ ጥቅሞች በኪታብ ላይ የተጻፉ ነገሮችን፣ የተለያዩ መጽሐፍት ላይ የተጻፉ ህጎችን፣ ትልልቅ ታሪኮችን… ጠቅለል ባለ ሃሳብና ልቦና ላይ በሚቀረጽ መልኩ ማስረዳት፣ ማስገንዘብ እና ማስተማር ነው ይላል፡፡ በመንዙማ ትልቅ ትምህርት ይሰጣል፡፡ የሚንጸባረቀው መልዕክትም የፈጣሪን ትእዛዝ መወጣትን፣ የቤተሰብን ሃቅ ማክበርን፣ በህይወት እያሉ የእናትና አባትን አደራ መወጣትን፣ አንድነትና አብሮነት ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ የመንዙማ ጥበብ ግለሰቦች ከጎረቤቶቻቸውና ከሚኖሩበት ማህበረሰብ ጋር ሊኖራቸው ስለሚገባው ጠንካራ ትስስር፣ መረዳዳትና መተጋገዝ በስፋት ያስተምራል። በመሆኑም መንዙማን እንደ አንድ የማህበራዊ መመሪያ መጽሐፍ አድርጎ መመልከት ይቻላል።

..ኧ…መገን፣ መገን፣ መገን

የሰው ልጅ ወገን፤ የሰው ልጅ ዘመድ

የነጃሺ ልጅ፤ የሰይድ ቢላል

የታሪክ ዓምዱ መች ዘመም ይላል

ይፈርሳል አትበል ምኑ ይፈርሳል

በፍትህ ማህበር ጸንቶ ቆሞ ሳል…የሚለው እና በሙንሺድ ወንድም ሷሊሕ “ሀገሬ” በሚል የተሰራው መንዙማ የሚያሳየውም ይህንኑ የሀገር አንድነትና አብሮነትን ነው፡፡

በእርግጥም የመቻቻልና የአብሮነት እሴቶች በመንዙማ ግጥሞች ውስጥ ጎልተው የሚታዩ ዋና ጭብጦች ናቸው። በሀገራችን የሚታወቀው  የመቻቻል ባህል በመንዙማ አማካኝነት ለትውልድ ሲተላለፍ ቆይቷል። ይህም ሰዎች እርስ በርስ በይቅርታና በአንድነት እንዲኖሩ በማሳሰብ፣ በማህበረሰቡ መካከል ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ በማስገንዘብ ረገድ ትልቅ አበርክቶ አለው።

በተጨማሪም መንዙማ በዕለት ተዕለት ህይወታችን ውስጥ ልንከተላቸው የሚገቡ ሥነ-ምግባሮችንና ልንተገብራቸው የሚገቡ በጎ ተግባራትን በዝርዝር ያስረዳል። በተቃራኒው ደግሞ ልንርቃቸው የሚገቡ መጥፎ ተግባራትን በማውገዝ፣ የሰው ልጅ ለፈጣሪውና ለወገኑ ታማኝ ሆኖ እንዲኖር ይመክራል።

ስለ ሞትና ስለ ዓለም አላፊነት የሚያስታውሱ የመንዙማ ስንኞች፣ ሰዎች በምድር ላይ በሚኖራቸው ቆይታ መልካም ስራን እንዲያበዙ ይገፋፋሉ። የነብዩ መሐመድን  ስብዕና፣ ሥነ-ምግባርና ማህበራዊ ትስስርን የተመለከቱ ታሪኮች በዜማ ተቀናብረው ሲቀርቡ፣ ሰዎች መልዕክቱን በቀላሉ ተረድተው በህይወታቸው እንዲተገብሩት ትልቅ እገዛ ያደርጋሉ።

መንዙማ ከመቻቻል፣ ከአብሮነት፣ ከይቅርታና ከሥነ- ምግባር አንጻር ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ነው። ጥልቅ የሆኑ ማህበራዊ እሴቶች በግጥምና በዜማ ተቀናብረው መቅረባቸው፣ መልዕክቱ በሰዎች ልብ ውስጥ ረጅም ጊዜ እንዲቆይ ያደርገዋል። ይህ የሀገር በቀል እውቀት ዛሬም ድረስ ለማህበረሰባዊ ሰላምና አንድነት እንዲሁም ፍትህ ግንባታ እንደ ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።

…ከፍ ዝቁን ተው ሁኑን እኩል በኩል

እስኪ አትናናቅ ወግ አትኮልኩል

የወንድምን ነፍስ ተው አትተንኩል… የሚለው የመንዙማ ስንኝ የሚያስረዳውና የሚያስተምረውም ይህንኑ ነው። የመንዙማና ነሽዳ ባለሙያ አሚር መሐመድ በበኩሉ ከዚህ ቀደም ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል በሰጠው አስተያየት መንዙማ ከሃይማኖትም ያለፈ ፋይዳ አለው፡፡ ትልልቅ የሀገር ባለውለታዎችን ለማስታወስ ይረዳል፡፡ የሀገር ፍቅርንም ይገልጻል፡፡ “ሃይማኖቱን በደንብ የሚያከብር ቤተሰቡን፣ ሀገሩን ያከብራል” የሚል መልክት በመንዙማ ይተላለፋል ይላል፡፡ ሁሉም ሃይማኖቶች የሚያዝዙት ደግሞ መከባበርን፣ አብሮነትን፣ ምክክርን፣ መዋደድን፣ ፍቅርንና መረዳዳትን ነው፡፡ ይህን በማንጸባረቅ ረገድ ደግሞ መንዙማ እጅግ ከፍተኛ ነው በማለት ያስረዳል፡፡

መንዙማ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም ማህበረሰቦች ዘንድም በዜማው ለዛና በግጥሙ ጥልቀት የሚታወቅ ጥበብ ነው። ለዘመናት በመውሊድ፣ በሰርግና በተለያዩ ማህበራዊ መድረኮች ላይ ሰዎች በጋራ እንዲሰበሰቡና የአንድነት ስሜት እንዲሰማቸው ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚህ አንጻር መንዙማ ኢትዮጵያ ለጀመረችው ሀገራዊ ምክክር ትልቅ አቅም መሆን የሚችል ሃብት ነው፡፡

ለሀገራዊ ምክክር ዋነኛው መነሻ  ፍትህን፣ ይቅርታን፣ አብሮነትንና አንድነትን መገንባት እንደመሆኑ መጠን፣ መንዙማ ሰዎችን በአንድ ጥላ ስር የማሰባሰብ ተፈጥሯዊ ኃይል አለው። በመንዙማ መድረኮች ላይ የሚታየው አውራጅና ተቀባይ  ሥነ ስርዓት፣ በራሱ የንግግርና የድምፅ ስምምነትን የሚያስተምር ነው። ይህ ደግሞ በሀገራዊ ምክክር ወቅት አንዱ ሌላውን እንዲያዳምጥ፣ የተለየ ድምፅ ያላቸው ወገኖች ደግሞ በጋራ ስምምነት ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ  እንደ ተምሳሌት መሆን የሚችል ስርዓት ነው፡፡

የማንኛውም ሀገራዊ ምክክር ማጠንጠኛ ያለፈውን ቁስል በይቅርታ መፈወስና ለወደፊቱ አብሮ ለመጓዝ መስማማት ነው። መንዙማ ደግሞ በይዘቱ የሰው ልጅን ሥነ- ምግባር  የሚያርሙ መልዕክቶችን ይይዛል። በውስጡ የሚገኙት የይቅርታ፣ የትዕግስትና የርህራሄ ስንኞች ለምክክሩ ሂደት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ናቸው።

መንዙማ  ቂም በቀልን መተው እና ለሰው ልጅ ክብር መስጠትን ቅድሚያ ይሰጣል። በመንዙማ ውስጥ በዋናነት የሚተላለፈው “የሰው ልጅ ሁሉ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር ይገባዋል” የሚለው ትልቅ መልዕክት በጠረጴዛ ዙሪያ ለሚደረግ ውይይት በጎ ተጽዕኖ ይኖረዋል። ይህን ሃሳብ የሚያጠናክርልን  የወንድም ሷሊሕ መንዙማ ነው፡፡

በሀገር ልጅ ለዛ ተዋደድ አንተው

እኛ ከእነሱ መባባሉን ተው

ታረቅ ከራስህ ታረቅ ከሰው…፡፡

መንዙማ ስለ ሀገር ሰላምና ደህንነት የሚጸለይበት (ዱዓ የሚደረግበት) መድረክ ነው። “አላህ ሀገራችንን ሰላም ያድርግልን” የሚለውና ሌሎች መሰል የሀገር ፍቅር መግለጫዎች በዜማ ሲቀርቡ፣ ዜጎች ከጎሰኝነትና ከጠባብነት ተላቅቀው ስለ ትልቋ ሀገር እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል።

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ውስጥ “ኢትዮጵያዊነትን” እና “የጋራ ማንነትን” ማጠናከር አንዱ ግብ ነው። መንዙማ የአገር በቀል ቋንቋዎችን በማቀናጀትና የአካባቢውን የዜማ ለዛ በመጠቀም፣ ልዩነትን እንደ ጌጥ የማየት ባህልን ያዳብራል። ይህ ደግሞ ምክክሩ “ልዩነታችንን አክብረን በአንድነትና በእኩልነት እንኑር” የሚለውን መርህ እንዲያሳካ ይረዳዋል።

በተጨማሪም መንዙማ በግጥሞቹ ውስጥ ስለ ማህበራዊ ኑሮ፣ ስለ ጎረቤት መብትና ስለ መረዳዳት በሰፊው ይተነትናል። አንድ ሰው ለብቻው ሳይሆን ከማህበረሰቡ ጋር ተሳስሮ መኖር እንዳለበት የሚያስተምሩት ስንኞች፣ ለምክክር ሂደቱ መሰረት የሆነውን አብሮነትና ፍቅርን፣ ይቅርታና አንድነትን ለመገንባት ያግዛሉ፡፡

መንዙማ ለሀገራዊ ምክክር፣ አብሮነትና አንድነት ያለው ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው። ምክንያቱም መንዙማ የመቀራረብ መድረክ፣ የይቅርታ ትምህርት ቤት፣ የሀገር ፍቅር መግለጫና የማህበራዊ ትስስር ማጠናከሪያ ነው። ይህ ሀገር በቀል ጥበብ ከዘመናዊው የምክክር ሂደት ጋር ቢቀናጅ፣ ኢትዮጵያ ለምትፈልገው ዘላቂ ሰላምና እርቅ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት ይችላል፡፡ 

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review