የዓድዋ ድል ታሪክ በተንቀሳቃሽ ምስል ወይም በፊልም ተሰንዶ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሰራል – አቶ ካሳሁን ጎንፋ

You are currently viewing የዓድዋ ድል ታሪክ በተንቀሳቃሽ ምስል ወይም በፊልም ተሰንዶ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር ይሰራል – አቶ ካሳሁን ጎንፋ

AMN- መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

የጥቁር ህዝቦች ድል የሆነዉ የዓድዋ ድል ታሪክ በተንቀሳቃሽ ምስል ወይም በፊልም ተሰንዶ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ትብብር እንደሚሰራ የአዲስ ሚድያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ተናገሩ።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በጋራ መስራት የሚያስችላቸዉን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

የመግባቢያ ስምምነቱን የፈረሙት የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ኤኤምኤን የአድዋን ድል ታላላቅ ታሪኮች አጉልቶ ከማውጣት፤ ለተቀረዉ አለም ከማስተዋወቅ እና ለቀጣዩ ትዉልድ እንዲተላለፍ ከማድረግ ረገድ በርካታ ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የመዲናዋ ዋንኛ የቱሪዝም መስህብ የሆነዉ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ እና ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በኋላም የአድዋን ታሪኮች በተለያዩ ቋንቋዎች ለህዝቡ ተደራሽ በማድረግ እና የጋራ ታሪክን በማጽናት ሃላፊነቱን በመወጣት ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ የአድዋ ድል ታሪክ በአግባቡ ተሰንዶ ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍበት ስፍራ መሆኑም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ተናግረዋል፡፡

የዓድዋ ድል ታሪክ በተንቀሳቃሽ ምስል ወይም በፊልም ተሰንዶ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ከማድረግ ረገድ የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ፤ ምሁራን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ሊሰሩ ይገባል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዉ ኤኤምኤንም ሃላፊነቱን እንደሚወጣ ገልጸዋል፡፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) በበኩላቸዉ አባቶቻችን ትልቅ ዋጋ ከፍለው የተከበረች ሀገር አውርሰውናል፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም ይህንን ታሪክ አጉልቶ ከማውጣት፤ ለተቀረዉ አለም ከማስተዋወቅና ለትውልድ እንዲተላለፍ ከማድረግ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም፤ አድዋና ህዳሴ የማይለያዩ ጉዳዮች ናቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እነዚህን የወል ታሪኮች በማስተዋወቅ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ሁለቱ ተቋማት የበለጠ ተቀራርበዉ ለመስራት የሚያስችላቸውን ፊርማ ማኖራቸውም ለከተማዋ ብሎም እንደ ሀገር ለተያዙ ትልሞች የሚጫወተው ሚና የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአለሙ ኢላላ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review