በመዲናዋ የተገነቡት የኮሪደር ልማቶች ነዳጅን ለመቆጠብ ትልቅ እገዛ እያደረጉ ነው

You are currently viewing በመዲናዋ የተገነቡት የኮሪደር ልማቶች ነዳጅን ለመቆጠብ ትልቅ እገዛ እያደረጉ ነው

AMN- መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የተገነቡት የኮሪደር ልማቶች ለእግረኞችና ለብስክሌት ተጠቃሚዎች ምቹ በመሆናቸው፣ አጫጭር መንገዶችን በእግር በመጓዝ እና ብስክሌቶችን በመጠቀም የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ እንደሚቻል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ስመኘው ተሾመ ገልጸዋል።

በመካከለኛው ምስራቅ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ ንረት እና የአቅርቦት እጥረት መከሰቱ ይታወሳል። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በስፋት መጠቀም ከነዳጅ ጥገኝነት ለመላቀቅ ሌላኛው አማራጭ እንደሆነም አቶ ስመኘው ተናግረዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም፣ ነዳጅ ከወደብ ተጭኖ ማደያ ጣቢያዎች እስኪደርስና ለተጠቃሚዎች እስኪሰራጭ ድረስ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በአዲስ አበባ የመኪና አሽከርካሪ የሆነው ህዳሴ ታሪኩ፣ በዓለም የተፈጠረውን የነዳጅ ቀውስ ለመቋቋም እንዲቻል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ም ዜጎች ነዳጅን በመቆጠብ እንዲጠቀሙ ያስተላለፉትን ጥሪ ተግባራዊ በማድረግ ነዳጅን በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ለማንኛውም አይነት እንቅስቃሴ መኪና ዋና አማራጫቸው መሆኑን እና አሁን ግን ተሽከርካሪዎችን የሚጠቀሙት ለወሳኝ ሥራና ጉዳዮች ብቻ አድርገው ነዳጅ ለመቆጠብ እየሞከሩ እንደሆነ አሽከርካሪዎቹ ተናግረዋል።

ሌላኛው አሽከርካሪ ዘመላክ፣ ብዙ መኪናዎች ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ መኪናዎችን በጋራ በመጠቀም እና በአንድ ተሽከርካሪ ተሰባስቦ በመንቀሳቀስ የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ ይችላሉ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎች ነዳጅን ለተጠቃሚዎች በሚያሰራጩበት ወቅት በመንግስት የወጡ መመሪያዎችን ተከትለው እየሰሩ መሆኑን ገልጸው፣ በጀሪካን፣ በበርሜል እና በተለያዩ ህገ-ወጥ መንገዶች የሚደረጉ የነዳጅ ሽያጮችን እንደማያስተናግዱ የነዳጅ ማደያ ሰራተኛ አቶ ገዛሐኝ ገብረሓና ተናግረዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review