የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ካሉ ተግባራት መካከል አንዱ አገልግሎት አሰጣጥ ነው። ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለው አመራር ሚና ትልቅ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ረቡዕና አርብ የባለጉዳይ ቀን ተብሎ ለአገልግሎት የሚመጡትን እንዲያስተናግድ መደረግ ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል፡፡ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ከዚህ አንጻር ያለው አሁናዊ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ቅኝት አድርጓል፡፡
ወይዘሮ ፅጌ መርሻ ይባላሉ፤ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 7 ነዋሪ ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ መኖር ከጀመሩ ከ45 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ በእድሜ አዛውንት የሚባሉ ናቸው፡፡ ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው በመሆናቸውና በቤት እጦት ምክንያት ኑሯቸውን ለመግፋት ቢያዳግታቸው በአካባቢያቸው ወደሚገኘው ወረዳ በማቅናት የቤት ጥያቄያቸውን በ2014 ዓ.ም አስገቡ፡፡ በዚህ ጊዜ ‘ጥያቄዎት ምን ነበር?’ ብሎ የሚያነጋግራቸው የመንግስት አካል አላጡም፡፡ የአራዳ ክፍለ ከተማ ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም ዋና ስራ አስፈፃሚ የመጣሁበትን ጉዳይ ጠይቀውኛል፡፡” በማለት ባለጉዳይ ሆነው የሄዱበትን ምክንያትና ከሚመለከተው አመራር የተደረገላቸውን አቀባበል አስረድተዋል፡፡
“ክፍለ ከተማው ችግሬን በመስማት እኔ እዛው ባለሁበት የሚመለከተውን የወረዳ አመራር ደውሎ አጣርቷል፡፡ ቤት እንደሌለኝ እና እንደተቸገርኩ ቀጠና ላይ የሚገኙ የኅብረተሰብ ተወካዮች የጻፉልኝ ደብዳቤ ህጋዊነት እንደሌለው ተነግሮኛል።” የሚሉት ወይዘሮ ፅጌ፤ ለመፍትሄው የተሰጣቸው አቅጣጫ፣ የደሀ ደሀ በሚል በድጋሚ ማመልከት እንደሚጠበቅባቸው ነው፡፡ ይህም ለእንግልት እንደዳረጋቸው ነግረውናል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ቤቶች ፅህፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ፅጌ ከተማ ባለጉዳዮች ላነሷቸው ቅሬታዎች በአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገቢውን ምላሽ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡ “ባለጉዳዮቻችን የኛ የሥራችን አንድ አካል ናቸው፡፡ ቅሬታቸውን በተለያየ አግባብ ቢያነሱም እንደ ተገቢነቱ እያስተናገድን ነው፡፡ የህግ አግባቡ መመሪያው በፈቀደለት ሁናቴ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የዝግጅት ክፍላችንም በቦታው ላይ ተገኝቶ በአንድ ማዕከል አገልግሎት ላይ ባለጉዳዮች ላነሱት ቅሬታ ተገቢውን ምላሽ እንዲያገኙ የሚደረግበት አግባብ እንዳለ ታዝቧል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከላይ በቤት እጦት ምክንያት ትልቅ እንግልት ውስጥ የነበሩት እናት መፍትሄ እንዲያገኙ ከማስቻል አንፃር የክፍለ ከተማው ቤቶች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፅጌ ወረዳ ድረስ በመደወል ጉዳያቸውን አጣርተው ተገቢውን ምላሽ መስጠታቸውን ተመልክቷል፡፡
ወጣት ኤፍሬም ስዩም ይባላል፡፡ “ኤፍሬምና ጓዶኞቹ” የተሰኘ ማሕበር በማቋቋም የፈጣን ምግብ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ መቀመጫቸውን በአራዳ ክፍለ ከተማ ያደረጉት እነኤፍሬም የሚሠሩበት ስፍራ ከተፈቀደው ውጪ ዳስ በመጣላቸው 5 ሺህ ብር የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል፡፡ ይህንን ውሳኔ መነሻ በማድረግ ቅሬታውን ለማቅረብ ወደሚመለከተው የመንግስት ተቋም መምጣቱን ያነሳል፡፡ የመሣሪያ ቦታቸው ለፀሐይ እጅግ የተጋለጠ በመሆኑ ተጠቃሚዎች ምቾት እንዳይነሳቸው፣ ሥራቸውም በፀሐይ ምክንያት እንዳይበላሽ በማሰብ ያደረጉት ስለመሆኑ ወጣት ኤፍሬም ተናግሯል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ለማነጋገር በባለጉዳይ ቀን መምጣታቸውንና የክፍለ ከተማው ስራ አስፈፃሚ፣ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ብሎም የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በተገኙበት የአንድ ማዕከል አገልግሎት ላይ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ችለዋል። በተሰጣቸው ምላሽም አሁን ላይ እንደ ከተማ የወረደ አቅጣጫን መሠረት በማድረግ ማንኛውም አካል ስራ እንዲሰራ ከተፈቀደለት ስፍራ ውጪ ዳስ መጣል አልያም ከመስሪያ ቦታ ውጪ ወንበሮችን ደርድሮ ተጠቃሚን ማስተናገድ እንደማይቻል በአራዳ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ወንድሙ ኡመር ተገልጾላቸዋል፡፡
ወይዘሮ አሰለፈች ቦኮ ይባላሉ፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ በተለምዶ 41 ኢየሱስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው። የመሬት ግብር ለመክፈል አስፈላጊውን መረጃ በመያዝ ወደ ክፍለ ከተማው ገቢዎች ጽህፈት ቤት መምጣታቸውንና ባገኙት አገልግሎት ተደስተው እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ፤ ካለምንም እንግልት ጉዳዬን ፈፅሜለሁ፡፡ በተለይ አመራሩ በባለጉዳይ ቀን የሰዎችን ጥያቄ ለመመለስ የሚሄድበትን ትህትናን የተላበሰ መስተንግዶ አድንቀዋል፡፡
ወይዘሮዋ፤ ከዚህ ቀደም የማመናጨቅና የማንገላታት ሁኔታ ይስተዋል ነበር። አሁን ላይ በዚህ ልክ ተስተካክሎ ማየታቸው አስደስቷቸዋል፡፡ ባለሙያው እራሱ ትህትና በታከለበት አግባብ “ጉዳዩ ምንድነው?” በማለት የሚጠይቅበት የሥራ ሥነ ምግባር እየተፈጠረ መጥቷል። አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን ስለመያዛችን ግልፅ በሆነ መንገድ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ‘ጉዳዬ በስንት ጊዜ ያልቅ ይሆን?’ ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ለመምጣቱ ዋነኛ ምክንያት ሰርቶ የሚያሰራ አመራር በስፍራው መገኘት መቻሉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ መሰረት ያየሽ ይባላሉ፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 2 ነዋሪ ናቸው፡፡ “የእድር ቤታቸው በልማት ፈርሶባቸው ተለዋጭ እንደሚሰጣቸው ቢነገራቸውም ላልተገባ ምልልስ መዳረጋቸውን ገልፀውልናል። ክፍለ ከተማው ጥያቄያችን ትክክል ስለመሆኑ ቢረዳም ጉዳዩን ግን ለማስፈፀም ዘግይቶብናል፡፡ ጉዳዩን በቅርበት የያዘው የክፍለ ከተማው ቤቶች ጽህፈት ቤትም በምላሹ ምንም አይነት ውክልና የሌላቸው የእድር አባላት መጥተው ጉዳዩን ማስፈፀም አይችሉም፡፡ ይልቁኑም ህጋዊ ውክልና ያላቸው ብሎም የእድር ሰብሳቢ የሆኑ ህጋዊ አካላት ናቸው ከምን ደረሰ ብሎ የመጠየቅ ብሎም የማስፈጸም መብት ያላቸው” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ገልጸውልናል፡፡
አቶ ማሙሽ አግዴ በየካ ክፍለ ከተማ ቤቶች ጽህፈት ቤት የይዞታ ማስተካከል ቡድን መሪ ናቸው፡፡ በርካታ ቁጥር ያለው የኅብረተሰብ ክፍል የመሬት ነክ ጉዳዮችን ይዞ ይመጣል፡፡ ቅሬታዎች የሚነሱባቸው አግባቦች የተለዩ መሆናቸውን ተከትሎ በየዘርፉ ያለ አመራር መፍትሄ እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡ “እንደ ክፍለ ከተማችን ተጨባጭ ሁኔታ በባለጉዳይ ቀን አመራሩ መስክና ስብሰባዎችን ከማድረግ ይልቅ ለሚነሱ ቅሬታዎች መፍትሄ የሚሰጥበት አግባብ ሰፊ ነው። የኮሪደር ልማት ሥራዎች በስፋት የሚከናወንበት አካባቢ መሆኑን ተከትሎ አመራሩ ጊዜውን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል እያገለገለ ይገኛል፡፡ በተለይም ከስራ ሰዓት ውጪ ባሉ ቀናት ጭምር የማኅበረሰቡን መረጃዎች በማደራጀት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል” ሲል ተናግሯል፡፡

በአካል ብሎም በፅሑፍ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን አመራሩ ብቻ ሳይሆን ታች ድረስ ያለ ባለሙያ ጭምር አጥጋቢ ምላሽ እየሠጠ ይገኛል፡፡ ይህን አይነቱን ግንዛቤ በባለሙያዎች ዘንድ እንዲፈጠር ከማድረግ አንጻር የተለያዩ የግንኙነት መድረኮች ላይ በግልፅ በመነጋገር መፍትሄ ላይ ስለመደረሱ ገልፀዋል። ባለሙያዎች ብሎም አመራሮች ከስራ ሰዓት ውጪ መሥራትን ባህል አድርገው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም በተለያዩ ጊዜያት ለሚነሱ ቅሬታዎች ከስር ከስር መፍትሄ እየሰጡ የመሄድ ባህልን እያዳበርን እንገኛለንም ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአገልግሎት አሰጣጥ አውትሶርስ ኃላፊ አቶ በቀለ ተመስገን ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፤ ከተማ አስተዳደሩ ረቡዕና አርብ የባለጉዳይ ቀን በሚል አመራሩ በቢሮው ተገኝቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ሲወሰን የራሱ የሆነ ዓላማ አለው፡፡ በቀጥታ ማኅበረሰቡ አመራሩን አግኝቶ ጉዳዩን እንዲያስረዳ እድል የሚፈጠርበት ነው ብለዋል፡፡
እንደ አቶ በቀለ ገለፃ፤ ተገልጋዩ ማኅበረሰብ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በቀጥታ የሚመለከተው አመራር ሌላ ሶስተኛ ወገን ሳያስፈልግ ውሳኔ ሰጪውን አካል እና የተቋሙን ኃላፊዎች በቀጥታ አግኝቶ ቅሬታቸውን ማቅረብ እና መፍትሄ ማግኘት እንዲችሉ ማስቻል ነው፡፡ ያቀረቡትን ጥያቄ ደግሞ አመራሩ አዳምጦ በመረዳት የታዩ የብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን እንዲፈታ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
አቶ በቀለ እንደተናገሩት፣ በ2016 ዓ.ም የባለጉዳይ ቀንን ተግባራዊነትና አፈፃፀሙን በተመለከተ ቅኝት ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህም ገና ልምምዱ አዲስ ስለነበር 63 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው አመራር ብቻ ነበር ቢሮ ላይ ቁጭ ብሎ ባለጉዳይን ሲያስተናግድ የነበረው፡፡ የተቋም ኃላፊዎችን ሰብስበን ማስተካከያ እንዲደረግ ተደርጓል፡፡ በዚህም ከዓመት ዓመት እንዲሁም በየሩብ ዓመቱ መሻሻሎችን ለማየት ተችሏል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት የግማሽ ዓመት አፈጻፀምን በተመለከተ 94 በመቶ የሚሆኑት ተሿሚ አመራሮች በባለጉዳይ ቀን ቁጭ ብለው አገልግለዋል፡፡ በተለያየ ሙያ የሚያገለገሉ ባለሙያዎች በተዋረድ 90 በመቶ የሚሆኑት ለተገልጋይ አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት መቻላቸውን ቢሮው ያደረገው የምልከታ ግኝት እንዳመላከተ አስቀምጠዋል፡፡
እንደ አቶ በቀለ ማብራሪያ፤ ቢሮ ተቀምጦ አገልግሎት ሰጠ አልሰጠ ብቻ የሚለው ነገር ብቻ በቂ አይደለም፡፡ “ህዝብን በምን አግባብ እያገለገለ ነው” የሚለውን ለመቃኘት ከተገልጋይ ጭምር እርካታ እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡ በተለይም የመማክርት ጉባኤ የተገልጋይ ካውንስል በሁሉም ተቋማት ላይ የተደራጀበት አግባብ አለ፡፡ በዚህም አገልጋዩ ከተገልጋዩ ጋር ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተት በማጥበብ ረገድ እገዛ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ በቀለ ገለፃ፤ እስካሁን በተሠራው ሥራ የተገኘው ውጤት የአገልግሎት አሰጣጡ በከተማ አቀፍ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ እመርታዊ ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ የክትትልና ድጋፍ አግባቦችን ካለመቆራረጥ የማድረግ እንዲሁም ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡ በተሠራው ሥራም መብቱን በአግባቡ የሚያውቅ ማኅበረሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡ በተለይም በአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠቃሚ የሆኑ አካላት አመራሩ ፊት ለፊት በመገኘት ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ መደረጉ ባለጉዳዩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲያገኝ ያግዘዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አመራሩ ለተነሱ ጥያቄዎች በቶሎ ምላሽ የመስጠት ባህሉን ማዳበር በመቻሉ ምክንያት ባለጉዳዮች እንዳይንገላቱ ብሎም ጊዜና ጉልበታቸውን እንዲቆጥቡ ያስችላቸዋል። ትክክለኛነት አልያም አግባብነት የሌለውን ጥያቄ ባለጉዳዩ በሚያነሳበት ወቅትም እዚያው የሚታረምበት አግባብ በመኖሩ ምክንያት የአመራሩንም የባለጉዳዩንም ጊዜ መቆጠብ ተችሏል፡፡
ከተገልጋዩ ማህበረሰብ ጉቦ አልያም እጅ መንሻ መቀበል ብቻ ሳይሆን፤ በተገቢው መንገድ ተገልጋዩን ማህበረሰብ አለማገልገል በራሱ ያስጠይቃል። የትኛውም አመራርም ሆነ ባለሙያ ተገልጋይን የሚያመናጭቅ ከሆነ ተጠያቂ ከመሆን አይድንም፡፡ በከተማ አቀፍ ደረጃ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት በተደረገው የአፈፃፀም ግምገማ መሠረት ቁጥራቸው 3 ሺህ 842 የሚሆኑ ከአመራሮች እስከ ታችኛው ባለሙያ ድረስ የሚገኙ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ተችሏል፡፡ አገልግሎትን በተገቢ አግባብ መፈፀም ያልቻሉ ቁጥራቸው ወደ 61 የሚጠጉ ተሿሚ አመራሮች፣ በዳይሬክተርና ቡድን መሪ ደረጃ 126 እንዲሁም ቁጥራቸው ወደ 3 ሺህ 542 ባለሙያዎች ተጠያቂ ስለመደረጋቸውም ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን