AMN መጋቢት 22/2018 ዓ.ም
የዓለም አቀፉ የትራንስፖርት ዘርፍ ከነዳጅ ጥገኝነት ተላቆ ወደ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያደርገው ሽግግር ከምንጊዜውም በላይ እየተፋጠነ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የቅንጦት ምርጫ መሆናቸው ቀርቶ ለአየር ንብረት ጥበቃ፣ ለኢኮኖሚ እድገትና ለከተሞች ጸጥታ ወሳኝ መፍትሔ ሆነው ብቅ ብለዋል። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ለነዳጅ ግዢ የሚወጣውን በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ለመታደግ ያላቸው ፋይዳ የጎላ መሆኑ ይነገራል።
በዓለም ላይ በዘርፉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠርና አጠቃቀሙን በማስፋፋት ፈር ቀዳጅ ከሚባሉ ሀገራት መካከል ኖርዌይ የዓለማችን ቀዳሚዋ የኤሌክትሪክ መኪና ተጠቃሚ ስትሆን፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ከሚሸጡ አዳዲስ መኪኖች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ መንግስት የግብር ነፃ መብቶችንና ነፃ የኃይል መሙያ ቦታዎችን በማመቻቸቱ ለዚህ ስኬት በቅታለች፡፡
ቻይና ደግሞ የራሷን ግዙፍ አምራች ኩባንያዎች (እንደ BYD ያሉትን) በማበረታታት እና በመላ አገሪቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን በመገንባት ግንባር ቀደም ሆናለች፡፡
አይስላንድ፣ ከኖርዌይ በመቀጠል በነፍስ ወከፍ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መኪና ተጠቃሚ ያለባት ሀገር ናት። ያላትን የተፈጥሮ ታዳሽ ኃይል ለመኪና በመጠቀሟ ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገች ትገኛለች።
ስዊድን፣ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ድረስ በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖችን ሽያጭ ለመገደብ አቅዳ እየሰራች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከሚሸጡ መኪኖች ግማሽ ያህሉ የኤሌክትሪክ ወይም ድብልቅ (Hybrid) ናቸው።
የመኪና ኢንዱስትሪ ማዕከል የሆነችው ጀርመን፣ እንደ ቮልስዋገን እና ቢኤምደብሊው ያሉ ታዋቂ ኩባንያዎቿ ወደ ኤሌክትሪክ መኪና አመራረት በማዘንበላቸው አጠቃቀሙ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ይገኛል።
በርካታ ሀገራት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋፋት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን እየተከተሉ ይገኛሉ ከነዙህም መካካል፤ የኃይል መሙያ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት፣የቀረጥ ቅናሽ እና ነፃ የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ማመቻቸት፣ የሚሞላው ኤሌክትሪክ ከታዳሽ የኃይል ምንጮች (ነፋስ፣ ፀሐይ ወይም ውኃ) እንዲሆን መስራት ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ይህ ዓለም አቀፋዊ እንቅስቃሴ የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየቀየረው ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያም በዘርፉ አመርቂ ለዉጥ በማስመዝገብ ላይ ከሚገኙ የአፍሪካ ሃገራት መካከል አንዷ መሆኗንም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ