AMN – ግንቦት 14/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ያለመው የ“ዱባይ-ኢትዮጵያ የቢዝነስ ትስስር” ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የንግድ መሪዎች እና ታዋቂ ባለሀብቶች ተገኝተዋል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያ እና ፓሲፊክ ጉዳዮች ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አምኃ ኃይለጊዮርጊስ በመክፈቻው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉትን አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በስፋት አብራርተዋል።
አቶ አምኃ አክለውም የኤሚሬት ባለሀብቶች ምቹ በሆኑት የግብርና፣ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የታዳሽ ኃይል፣ የሎጅስቲክስ፣ የቱሪዝም እና የዲጂታል አገልግሎት ዘርፎች ላይ በስፋት እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር በበኩላቸው፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል እያደገ የመጣው ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለግል ዘርፉ ሰፊ የገበያ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም የኤሚሬትስ ባለሀብቶች በአሁኑ ወቅት ምቹና ተወዳዳሪ እየሆነ የመጣውን የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ምህዳር በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አበረታተዋል።
የዱባይ ንግድ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት እና ዋና ስራ አስፈፃሚ መሐመድ አሊ ራሺድ ሉታህ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን ስትራቴጂካዊ የንግድና ኢንቨስትመንት ማዕከልነት አጉልተው ጠቅሰዋል።
ሀገራቸው እምቅ አቅም ካላት ኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት ይበልጥ ለማስፋት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላትም አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች አምባሳደር ራሺድ አብዱላህ አልሸሂ እንደገለጹት በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል የላቀና የጎላ የንግድ ተሳትፎ እንዲኖር ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና አጋር ተቋማት በሀገሪቱ ስላሉት የኢንቨስትመንት ዕድሎች፣ መንግስት ስላዘጋጃቸው ማበረታቻዎችና ስለተወሰዱት የማሻሻያ እርምጃዎች ለታዳሚዎቹ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
ይህ የቢዝነስ ፎረም የሁለቱን ሀገራት የባለብዙ ወገን የንግድ ልውውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ቁልፍ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።