AMN- መጋቢት 22/2018 ዓ.ም
ለዘመናት የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ድክመት ለመግለጽ “ኢትዮጵያ መርፌም የማታመርት ሀገር ናት” የሚለው ተስፋ አስቆራጭ ንግግር በተደጋጋሚ ይደመጥ ነበር።
ይህ አባባል የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዝቅጠትና በኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ያላትን ፍጹም ጥገኝነት የሚያሳይ የቁጭት መግለጫ ሆኖ ቆይቷል። ነገር ግን ዛሬ ላይ ያ የታሪክ ጠባሳ እየተሻረ፣ አዲስ የብሩህ ተስፋ ምዕራፍ እየተከተበ ይገኛል።
የሀገር በቀል እውቀትና የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ትስስር፣ በመንግስትና በግል ባለሀብቱ ጥረት ታጅቦ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ገጽታ በአስተማማኝ ሁኔታ እየቀየረው ነው። በተለይም “ኢትዮጵያ ታምርት” የተሰኘው ሀገራዊ ንቅናቄ ዝም ብሎ የቃላት ድርድር ሳይሆን፣ በተግባር የተፈተነና የአምራች ዘርፉን የልብ ትርታ የቀየረ ስትራቴጂካዊ መሳርያ ሆኗል።

ዛሬ ኢትዮጵያ ከቀላል የቤት ውስጥ መገልገያዎች እስከ ውስብስብ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ድረስ በስፋት ማምረት የጀመረችበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። በግብርና ውጤቶች ማቀነባበር ዘርፍ ሰፊ የግብርና ሀብትን ወደ ተጨባጭ ኢንዱስትሪ የለወጠ እና የገቢ ምርቶችን በከፍተኛ ሁኔታ የተተካበት ነው።
በምግብ ዘይት፣ ዱቄት፣ ፓስታና ማኮሮኒ የመሳሰሉት ምርቶች በሀገር ውስጥ ስንዴ ምርት እድገት ታግዘው በርካታ ፋብሪካዎች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን እያቀረቡ ነው። በታሸጉ ምግቦችና በወተት ተዋጽኦዎች ዘርፍም ስጋ፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም አይብና ቅቤ ተቀነባብረው ደረጃቸውን ጠብቀው ለገበያ እየቀረቡ ነው።
በኮንስትራክሽንና የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዘርፍ እንደ ሲሚንቶና፣ ብረት፣ የፕላስቲክ ቧንቧዎችና የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ ለውሃ ለፍሳሽ ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ የሚሆኑ ግብዓቶች በብዛት በሀገሪቱ ይመረታሉ።

የጨርቃጨርቅ፣ አልባሳትና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንድትሆን ካደረጓት ግንባር ቀደም መስኮች አንዱ ነው። በሀገሪቱ በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚመረቱ የተለያዩ አልባሳት ለአፍሪካና አውሮፓ ገበያዎች ጭምር እየተላኩ ነው።
የተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያና የኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ ሌላው ኢትዮጵያ ወደ ላቀ የቴክኖሎጂ ምዕራፍ መሸጋገሯን የሚያሳይ ትልቅ ማሳያ ነው። የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በቅርብ ጊዜያት በተወሰደው ፖሊሲ መነሻነት በርካታ የኤሌክትሪክ መኪናዎችና የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች በሀገር ውስጥ እየተገጣጠሙ ለገበያ እየቀረቡ ይገኛሉ።
የተለያዩ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የሞባይል ስልኮችን እዚሁ በመገጣጠም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ነው። የቤት ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች እንደ ቴሌቪዥኖች፣ ማቀዝቀዣዎች እና የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች በሀገር ውስጥ እየተገጣጠሙ ይገኛሉ።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከነበረችበት “መርፌ እንኳን የማታመርት ሀገር” ከመባል ሀፍረት ወጥታ ዛሬ አውቶቡሶችን፣ የኤሌክትሪክ መኪኖችንና ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚተርፉ አልባሳትን ወደ ማምረት መሸጋገሯ የታሪክ ስብራትን የጠገነ ታላቅ እምርታ ነው።
እርግጥ ነው ጉዞው ገና ብዙ ይቀረዋል፣ በቀጣይነትም ለነዚህ ኢንዱስትሪዎች የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ በስፋት ማምረት ላይ ትኩረት ከተደረገ፣ የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ እድገት ይበልጥ ፈጣንና አስተማማኝ እንዲሁም ተስፋ የሚጣልበት ይሆናል።
በይታያል አጥናፉ