AMN – መጋቢት 23/2018 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ከውበት መጠበቂያነት ባለፈ በተለያዩ አደጋዎችና በበሽታ ምክንያት የሚጎድሉ የሰውነት ክፍሎችን መልሶ በመገንባት የዜጎችን የሕይወት ጥራት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
በአለርት ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የፕላስቲክ ሪኮንስትራክቲቭ እና ማይክሮ ሰርጀሪ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር አብዱረዛቅ ዓሊ መሐመድ የዘርፉን ፋይዳ አስመልክተው ለኤ ኤም ኤን ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ዋነኛ ትርጉሙ አንድ የጎደለ ወይም በአደጋ ምክንያት መደበኛ ስራውን ማከናወን የተሳነውን የሰውነት ክፍል መልሶ በመስራት ወደ ተግባር መመለስ ነው።
ይህ የሕክምና ሂደት በዋነኝነት የሚከናወነው ከባለቤቱ ሰውነት ላይ ቆዳ ወይም ስጋ በመውሰድ ሲሆን፣ አልፎ አልፎም እንደ አስፈላጊነቱ ሰው ሰራሽ አካላትን በመጠቀም የጎደለውን ክፍል የመተካት ስራ ይከናወናል።

ዶክተር አብዱረዛቅ አክለውም፤ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ዋነኛ ዓላማ የውበት ወይም የቅንጦት ሳይሆን፤ የሰውን ልጅ የህይወት ጥራት ማሻሻል መሆኑን አስገንዝበዋል።
በአገራችን በስፋት የሚሰጡ የፕላስቲክ ቀዶ ህክምና ሕክምናዎች በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች የሚመደቡ ሲሆን፣ የመጀመሪያው ከተፈጥሮ ጋር ተያይዘው የሚመጡ እንደ ከንፈርና ላንቃ ስንጥቅ እንዲሁም በእጅ ላይ የሚታዩ መጠባበቆችን የማስተካከል ስራ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም በትራፊክ አደጋ፣ በቃጠሎና መሰል አጋጣሚዎች የሚከሰቱ የቆዳ መላጥን፣ የአጥንት መሰበርንና የፊት አካላት መጉደልን መልሶ የማስተካከል ሕክምና በስፋት ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳል።
ዘርፉ በካንሰር ሕክምና ውስጥ ያለውን ከፍተኛ ድርሻ ያብራሩት ስፔሻሊስቱ፣ በተለይም ከአንገት በላይ የሚከሰቱ የቆዳ ካንሰሮችን ከተወገዱ በኋላ የሚፈጠረውን ክፍተት የመተካትና በካንሰር ምክንያት የተቆረጡ የጡት ክፍሎችን መልሶ የመገንባት ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ማይክሮ ሰርጀሪን በመጠቀም የተቆረጡ የደም ስሮችን፣ ነርቮችንና የሰውነት ክፍሎችን መልሶ የመቀጠል ስራ በአለርት ሆስፒታልና በሌሎች የሪፈራል ማዕከላት በስፋት እየተሰጠ እንደሚገኝም ባለሙያው ተናግረዋል።
በበረከት ጌታቸው