መጋቢት – ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ጨምሮ ድለላን፤ አድልዎን እና እንግልትን በማስወገድ ለነዋሪዎች ግልጽ እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ፍሬ ያፈራበት ወር

You are currently viewing መጋቢት – ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን ጨምሮ ድለላን፤ አድልዎን እና እንግልትን በማስወገድ ለነዋሪዎች ግልጽ እና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ፍሬ ያፈራበት ወር

AMN_መጋቢት 22/2018 ዓ.ም

ማህበረሰቡ በተደጋጋሚ ከሚያነሳቸዉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መካከል የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተገልጋዮችን የሚያስተናግዱበት የአሰራር ሥርዓት ግልጽ እና ቀልጣፋ አለመሆን በቀዳሚነት ይነሳል፡፡

አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ረጅም ሰአት መጠበቅ፤ ለቀናት፤ለሳምንታትና ለወራት መመላለስ አልፎም ጉዳይን ለማስፈጸም የእጅ መንሻ መስጠት፤ዘመድ እና ደላላ ማፈላለግ የተቋማት መገለጫ እስኪመስል ድረስ ዋንኛ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡

ከለዉጡ በፊት በተለይ አዲስ አበባን በመሰሉ ትላልቅ ከተሞች ወደ መንግስት ተቋማት ጎራ ብሎ አንድን ጉዳይ ማስፈጸም በፍጹም የማይሞከር ተግባር ሆኖ ቆይቷል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ ለሙስናና ለብልሹ አሰራሮች የተጋለጠ በመሆኑ በህዝብና በመንግስት መካከል ትልቅ ቅሬታን ከመፍጠሩም በላይ ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለዉን አመኔታ እስከማሳጣት ደርሷል፡፡

የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ግልጽና ቀልጣፋ አለመሆን በሰላም፤ በልማትና እና በመልካም አስተዳደር ሥራዎች ላይ ከፍተኛ እንቅፋት መፍጠሩን የተረዳዉ የለውጡ መንግስት “አዲስ መሶብ” የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በአራዳ እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች ቀድም ብሎ ሥራ ያስጀመራቸው ሁለት ማዕከላት ከ120 ሺህ በላይ ደንበኞችን ያስተናገዱ ሲሆን ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑ ተገልጋዮች በአገልግሎቱ መርካታቸውን ገልጸዋል፡፡

በቅርቡ የተመረቀዉ የቂርቆስ ቅርንጫፍ አዲስ የመሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት 20 ተቋማት፣ በ85 የአገልግሎት መስኮቶች፣ 112 የተለያዩ የሕዝብ አገልግሎቶችን በአንድ ስፍራ ለተገልጋዮች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

የለውጡ መንግስት በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን፣ታአማኒ፣ፍትሐዊ ተደራሽና የመንግስት አገልግሎቶችን ለመስጠት መሰል ማዕከላትን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ ግንባታዎችን እያከናወነ ይገኛል።

ማዕከላቱን በመመረቅ ስራ ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ “አዲስ መሶብ” የአንድ ማዕከል ዲጂታል አገልግሎት የመንግሥት አገልግሎትን በማላቅ፤ ደላላን ፣ ሌብነትን፣ አድሎ እና እንግልትን በማስወገድ፣ ተደራሽነትን እና የዜጎችን እርካታ በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በተቋማት መካከል የነበረውን የተበታተነ አገልግሎት በማቀናጀት እንዲሁም ኅብረተሰቡ አገልግሎት ለማግኘት የሚያጠፋውን ጊዜና ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነስ ፍትሐዊ አገልግሎት እያሰፈነ ይገኛል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review